ስምምነቱ የደላላ የኋላ ቢሮ እና ትዕዛዝ አስተዳደር ስርዓትንንም የሚገነባ ነው ተብሏል።
ስምምነቱ ለገበያው ብርታት የሚሰጥና ወደፊት የሚያራምደው መሆኑን ሰምተናል።
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያውን በቴክኖሎጂ ለማቀላጠፍ ቴክኖሎጂ ከሚያቀርብልኝ ድረጅት ጋር አብሬ ለመስራት ተስማምቻለሁ ብሏል።
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ኢንፎቴክ ፕራይቬት ሊሚትድ ከተባለ የቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያ ጋር ነው አብሮ ለመስራት የወጠነው።
የተደረጉት ስምምነቶች ሁለት መሆናቸው ተሰምቷል።
እነዚህ የቴክኖሎጂ ስርአቶች ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ግልፅ የሆነ የሰነደ መዓለ ንዋይ ገበያ በኢትዮጵያ እንዲቋቋም ያግዛል ተብሏል።
የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ንግድን ለማቀላጠፍ እና አጠቃላይ የገበያውን መሰረተ ልማት ለማሳደግ ስምምነቱ በብርቱ ያግዛል ሲል የገበያው አቅራቢ ተናግሯል።

የኤሌክትሮኒክ መገበያያ መድረክ ቀጥተኛ የሆኑ ግብይቶችን ማስተናገድ የሚችል እጅግ ዘመናዊ የንግድ ከባቢን እንደሚፈጥረም ሰምተናል።
ይህ የቴክኖሎጂ ሲስተም ወደ ስራ ሲገባ የገበያ ግልፅነትን በማረጋገጥ፣ የፋይናንስ አቅምን ያሻሽላል ተብሏል።
ለሃገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ባለሃብቶችም አስተማማኝ የሆነ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ግብይት እንዲኖራቸው ያግዛል ተብሏል።
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ይህንን የቴክኖሎጂ ስርአት በመዘርጋት ኩባንያዎች ካፒታላቸውን በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲያሳድጉ ያግዛል ሲል ተናግሯል።
ከዚ ባለፈም በዚህ ስርአት አዳዲስ የኢንቨስትመንት እድሎችንም
ለህዝብ በማቅረብ የኢኮኖሚ እድገት አንቀሳቃሽ እንዲሆኑ ለማስቻል በሚደረገው ጥረት ከፊት እንደሚሆን ተናግሯል።
የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ደላላ የኋላ ቢሮ እና ትዕዛዝ አስተዳደር ስርአትም የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ድርጅቶችን አሰራር ለማቀላጠፍ እና ለማደራጀት የተዘጋጀ ሥርዓት ነው ተብሏል።
ይህ ሥርዓት ኢንቨስተሮችን ተቀብሎ የመመዝገብ፣ ትዕዛዞችን የመቀበል፣ ሪፖርት የማድረግ፣ ግብይትን ማቀነባበር እና የመሳሰሉትን ዋና ዋና ተግባራትን እንደሚያስተናግድ ተሰምቷል።
ከዚህም በተጨማሪ ይህ ሥርዓት የተለያዩ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያዎችን እና በበይነ መረብ ላይ የተመሰረቱ መስተጋብሮችን በማካተት ኢንቨስተሮች ግብይት እየተከናወነ በሚገኝበት ወቅት የመመልከት እድሉ እንዲኖራቸው ያግዛል።
በተጨማሪም በቀጥታ ትዕዛዝ መስጠት እንዲችሉ ያስችላቸዋል ተብሏል።
ይህንን ስርአት ወደ ስራ በማስገባት፤ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ላይ የተሰማሩ ደላሎች፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ አከናዋኞችና በእነዚህ አገልግሎቶች ውስጥ ለመሳተፍ ፍቃድ ያላቸው የኢንቨስትመንት ባንኮች በተሻለ ብቃት እና ትክክለኛነት እንዲሰሩ ያስችላል መባሉን ገበያ አቅራቢው አስረድቷል።
ስርአቱ ኢንቨስተሮችም በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያው ላይ ቀጥተኛ የሆነ ምልከታ ለማድረግ የሚያስችላቸው ሆኖ እንደሚዘጋጅም ሰምተናል።
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ጥላሁን እስማዔል “ይህ ስምምነት በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ለማቋቋም የያዝነውን ራዕይ እውን ለማድረግ እየሰራን መሆኑን የሚያስረዳ ትልቅ ምዕራፍ ነው” ብለዋል።
ተህቦ ንጉሴ
Comentários