top of page

ነሐሴ 8፣2015 - የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ የሚቆይ እንዲሆን ተጠየቀ


በአማራ ክልል የታወጀውና ዛሬ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ የሚቆይ እንዲሆን ተጠየቀ፡፡


ጥያቄውን ያቀረበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ነው፡፡


ኮሚሽኑ በአዋጁ ላይ የሰብአዊ መብቶች ትንታኔ እና ዝርዝር ምክረ ሀሳቦችን ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ልኬያለሁ ብሏል፡፡


ኮሚሽኑ ለምክር ቤቱ በላከው የትንታኔ ሰነድ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተለይም በአዋጁ የተመለከቱ ክልከላዎችና ግዴታዎችን እንዲሁም ለመንግስት የተሰጠውን የአስቸኳይ ጊዜ ስልጣን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቶበታል፡፡


የአዋጁን ከባቢያዊ እና የጊዜ ተፈፃሚነት ወሰን በተመለከተና የህዝብ ተወካዮች እንዲሁም ዳኞችን ያለ ምክር ቤቱ ውሳኔ ያለ መከሰስ ልዩ መብትን ጨምሮ ሌሎችም ሊገደቡ ስለማይችሉ መብቶች ጥበቃ እንዲደረግ የሚጠይቅ ዝርዝር ሰነድ ነው፡፡


በዚሁ ሰነድም በክልሉ ተከስቶ የነበረው የሰላምና ደህንነት ልዩ አደጋ በአሁኑ ወቀት ተወግዶ መደበኛ እንቅስቃሴው ወደነበረበት እየተመለሰ መሆኑን መንግስት በይፋ መግለፁን ጠቅሶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሳምንታት ቢበዛ ከ1 ወር ጊዜ የበለጠ እንዳይሆን ጠይቋል፡፡


ተፈፃሚነቱም ልዩ አደጋው ተከስቷል በተባለበት ቦታ ብቻ የተገደበ እንጂ በጠቅላላ ሃገሪቱ እንዳይደረግ ኮሚሽኑ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል፡፡


በተጨማሪም ከአዋጁ ጋር የሚቃረኑ የተባሉ የፍሬ ነገር እና የሥነ-ሥርዓት ህጎች በጅምላ ታገዳቸው እና ልዩ መብቶ ጥብቃዎች መታገዳቸው ትክክል ባለመሆኑ ምክር ቤቱ እንዲያጤነው ጠይቋል፡፡


ይህ የአዋጁ የጅምላ እግድ ያስከትላል ያለውና ውጤትም ኮሚሽኑ ለምክር ቤቱ በተላከው ሰነድ አብራርቷል፡፡


እንደምሳሌም የፓርላማ አባላትና የዳኞችን ያለ ምክር ቤቱ ውሳኔ ያለመያዝ ያለመከሰስ መብቶችን ጨምሮ ያላግባብ ለማገድ በር ክፍቷል ብሏል፡፡


በማንኛውም ጊዜ ብቁ፣ ነፃ እና ገለልተኛ የዳኝነት አካላት እንዲሁም የፍትህ ሥርዓት መኖር ለህጋዊነትና ለህግ የበላይነት መርህዎች መተግበር የግድ የሚል ነው ያለው ኮሚሽኑ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታም የዳኝነት ተቋሙ ተግባርና ሀላፊነት በሙሉ ነፃነት ሊቀጥል የሚገባው መሆኑን አሳስቧል፡፡


የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ነጥቦችን ያካተተውን ምክረ ሀሳብ ምክር ቤቱ አዋጁን ከማፅደቁ በፊት ሊያጤናቸው ይገባል ብሏል፡፡


የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ዛሬ ከሰዓት በኋላ ቀርቦ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡



ትዕግስት ዘሪሁን



የሸገርንወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Website: https://www.shegerfm.com/


Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il

Comments


bottom of page