ባለፉት 5 ዓመታት በተለይ በክረምት ወራት የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን ለመሸፈንና በሌላውም አካባቢ በዘመቻ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ሲተከሉ ቆይቷል።
በእነዚህ ዓመታት 32 ቢሊዮን ችግኝ ቢተከልም የህዝቡ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የደን መጨፍጨፉን አላስቀረውም።
ጥናቱን ያደረጉት ሁለት ፊንላንዳዊያን በኢትዮጵያ ደንን መጨፍጨፍ የተጀመረው በ16ኛው ክፍለ ዘመን መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከ1950 ጀምሮ ደግሞ በየዓመቱ እስከ 800,000 ሄክታር መሬት ደን ለማገዶና ለእርሻ በሚል ይጨፈጨፍ እንደነበር ጥናቱ ያሳያል፡፡

የግብርና ሚኒስቴርም ይህንን መነሻ በማድረግ ባጠናው ጥናት በየጊዜው ባለው የቴክኖሎጂ መስፋፋት ኤሌክትሪክ የሃይል ምንጭ እየሆነ በመምጣቱ ጭፍጨፋው መጠኑ መቀነስ ማሳየቱን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ባለፉት 13 ዓመታትም በየዓመቱ የሚጨፈጨፈው 92 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን እንደነበርና ችግኝ በመተከሉ ምክንያት ቀንሶ፣ በአሁኑ ወቅት 27,000 ሄክታር ደን በየዓመቱ እንደሚጨፍ ጥናቱን ዋቢ አድርገው የግብርና ሚኒስትር ዴኢታ ኢያሱ ኤሊያስ(ፕ/ር) ተናግረዋል።
የሚጨፈጨፈውን ለማካካስ ብዙ ችግኝ መትከል እንዲሁም ግንዛቤን ማስፋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የህዝብ ቁጥሩ እየጨመረ በመምጣቱ የደን ጭፍጨፋ ስጋት ሆኖ መቀጠሉ ስለማይቀር ህዝቡ ችግኝ ሲተክል አብዛኛው ለምግብነት የሚያውለው እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል፡፡

አረንጓዴ አሻራ በሚል ለዓመታት በተራቆቱ አካባቢዎች ችግኝ የተተከለው ችግኝ በስነ ምህዳሩ ላይ ምን ለውጥ አመጣ? በሚል በፕላንና ልማት ኮሚሽን አዘጋጅነት በተካሄደው ምክክር ከመትከል ባለፈ እንዴት እንከባከበው፣ የተራቆቱት የትኞቹ ናቸው በሚል ለይቶ መትከል እንደሚያስፈልግም ከተሳታፊዎች ተነስቷል፡፡
በጊዜ ተደርሶበት ችግኝ ከመትስከል ጀምሮ አስፈላጊው የስነ ምህዳር ጥበቃ ካልተደረገለት በአሁኑ ወቅት 11 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለረጅም ጊዜያት ተራቁቶ የቆየ በመሆኑ ለበረሃማነት መጋለጡም ተጠቅሷል፡፡
የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ተመራማሪው ግዛቸው ካቢቴ(ዶ/ር) በበኩላቸው መስሪያ ቤታቸው በየጊዜው የሚተከሉ ችግኞች በሳተላይት ምስል በሚደርሳቸው መረጃ መሰረት እንደሚከታተሉና የለሙና በረሃማ አካባቢዎችን በመለየት እየሰሩ እንደሆነ ነግረውናል፡፡
አረንጓዴ አሻራ በሚባለው መርሃ ግብር በ5 ዓመታት ከተተከሉት 32 ሚሊዮን ችግኞች 80 በመቶዎቹ መፅደቃቸውን የሚናገሩት አቶ ሃይሉ 40 በመቶዎቹ ችግኞች ለአካባቢ ጥበቃ የሚረዱ 60 በመቶዎቹ ለምግብነት የሚውሉ ናቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ስነ ምህዳሩን ለመጠበቅ ብሎም በምግብ እራስን ለመቻል ይውላሉ ብላ በየዓመቱ ችግኞችን እየተከለች ቢሆንም ለዚህ ስራ አጋዥ ናቸው ከተባሉት ሃገራት የሚሰጠኝ የገንዘብ ድጋፍ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብላለች፡፡
በመሆኑም ወጪውን በራስ አቅም ለመሸፈን ሲባል በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚፀድቀው አጠቃላይ በጀት 1 በመቶውን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሚሰሩ ስራዎች እንዲውል ለማድረግ የፖሊሲ ረቂቅ ተዘጋጅቷል፡፡
በቀጣዩ ዓመት በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት እንደሚፀድቅ ይጠበቃል መባሉን ሰምተናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments