ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ እና የክፍያ ስርአትን ለማዘመን የሚሰራው ሳንቲም ፔይ ፋይናንሺያል ሶሉሽን አ.ማ በመጪው ዓመት ከ10,000 በላይ ፖስ ማሽኖችን ለማሰራጨት አቅጄ እየሰራሁ ነው አለ፡፡
በተለያዩ የመገበያያ ቦታዎች ክፍያዎችን በዲጂታል እንዲከወኑ የሚያግዙ ወይም ለግብይት የሚያገለግሉ ፖስ ማሽኖችን በ2017 በጀት ዓመት ከ10,000 በላይ የሚሆኑ ማሽኖችን ለማሰራጨት ተዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡
ድርጅቱ ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ ከ1000 ማሽኖች በላይ አከፋፍሎ ስራዎችን ሲከውን መቆየቱን ሰምተናል፡፡
ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፉ በበቂ ሁኔታ አለመበርታ ተደጋግሞ የሚነሳ ጉዳይ ቢሆንም ሳንቲም ፔይ ፋይናንሺያል ሶሉሽን ወደ ስራ ያስገባውን ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የክፍያ ስርአትን ላይ ግን ተጠቃሚው ከፍተኛ ነው ይላሉ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ትንሳኤ ደሳለኝ፡፡
ዲጂታል የግብይት ስርአትን ለማዘመን እየሰራ መሆኑን የሚናገረው ሳንቲም ፔይ ፋይናንሺያል ሶሉሽን ከሁለት አመት በፊት ወደ ስራ ሲገባ በቀን ውስጥ ይንቀሳቀስ የነበረው የገንዘዘብ መጠን 20000 ብር መሆኑን የተናገሩት አቶ ትንሳኤ አሁን ከ100,000,000 ብር በላይ በቀን እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነግረውናል፡፡
እንዲህ አይነት መተግበሪያዎች ወደ አገልግሎት ሲገቡ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች አንዱ የኔትዎርክ መቆራረጥ እንደሆነ የሚናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው ይህንን ችግር ለመፍታትም እየተከወኑ ስላሉ ስራዎች ነግራናል፡፡
ሀምሌ ወር 2014 ዓ.ም ወደ ስራ የገባው ሳንቲም ፔይ ፋይናንሺያል ሶሉሽን አ.ማ ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የክፍያ ስርአትን በመፍጠር 11 ባንኮች ጋር በጋራ እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡
በሁለት አመታት ውስጥም ከ1 ሚሊየን በላይ ደንበኞች አገልግሎቱን እየተጠቀሙት እንደሆነ ድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ትንሳኤ ደሳለኝ ነግረውናል፡፡
ፋሲካ ሙሉወርቅ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments