top of page

ነሐሴ 6፣2016 - ‘ፍሪኤል ኢትዮጵያ’፤ በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል ባለማግኘቱ ከሌሎች ሀገራት ባለሞያዎችን ለማምጣት እየተገደደ መሆኑን ተናገረ

በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራው ‘ፍሪኤል ኢትዮጵያ’፤ በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል ባለማግኘቱ ከሌሎች ሀገራት ባለሞያዎችን ለማምጣት እየተገደደ መሆኑን ተናገረ፡፡


‘ፍሪኤል ኢትዮጵያ እርሻና ማቀነባበሪያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር’፤ አሁን እንዲያለማው ከተሰጠው 10,000 ሄክታር መሬት በተጨማሪ በሚቀጥሉት ዓመታት ተጨማሪ 20,000 ሄክታር መሬት ከመንግስት ለመውሰድ አቅዷል፡፡


ይህንን እቅዱን ለመፈፀም ሀገሪቱ ውስጥ በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት ችግር አለ ያሉት የፍሪኤል ኢትዮጵያ እርሻና ማቀነባበሪያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ቢዝነስ ኦፕሬሽን ማናጀር፤ አቶ ፋሲካ ስዩም በተለይም የተማረ የሰው ኃይል አቅርቦት እጥረት አጋጥሞናል ብለዋል፡፡


ማህበሩ ዋንኛ የገበያ መዳረሻዎቹ አውሮፓ ቢሆንም፤ ይህንን መስፈርት አሟልቶ ምርት ለማምረት የሚያስችል ባለሞያ በበቂ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ስላልተገኘ ከደቡብ አፍሪካ እና ከሌሎች ሀገራት ባለሙያ ለማምጣት እንደተገደዱ እንደሆነ አቶ ፋሲካ አስረድተዋል።


ፍሬል ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር እየሞከረ ነው ያሉት አቶ ፋሲካ ለአብነትም የድሮን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተለያዩ የኬሚካል እርጭቶችን እያደረገ ነው፡፡


ማህበሩ ምርቶችን በፍጥነት ወደተለያዩ መዳረሻዎች ለማጓጓዝ የሚረዳ የአውሮፕላን ማረፊያ እየገነቡ መሆኑን የሚያስረዱት ኃላፊው ነገር ግን አንዳንድ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር ሲሞከር የሚመለከታቸው አካላት ስራዎቹን ከመደገፍ ይልቅ ከዘርፉ ጋር አይሄድም በሚል ድጋፍ ሲነፍግ ይታያል ብለዋል፡፡


መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ከደረገ እና መሰረተ ልማቶችን በሚፈለገው ፍጥነት ከሟላ ፍሪኤል ኢትዮጵያ የዘይት ፋብሪካ ለማቋቋም ውጥን አለው ያሉት አቶ ፋሲካ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የተመቸ የግብርና ኢኮሎጂን በመጠቀም ሀገሪቱ ውስጥ የሚታየው የሽንኩርት ችግር ማህበሩ ብቻውን የመፍታት አቅም እንዳለው አስረድተዋል፡፡


የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የሆልቲካቸር ዘርፍ ችግርን በተመለከተ የ10 ዓመት ፖሊሲ ለማፅደቅ እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡


የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ፤ በፖሊሲው ዙሪያ ከዚህ በፊት በተደረገ ውይይት እንዳሉት ይህ ፖሊሲ በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾችን እና ባለሀብቶች የሚያነሱትን ችግር እንዲቀርፍ ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡


የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በበኩሉ ብቁ የሰው ኃይል ለአምራች ዘርፉ ለማፍራት ከተለያዮ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ቴክኒክና ሞያ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን በተደጋጋሚ ይናገራል፡፡


በረከት አካሉ



Comments


bottom of page