በተለያዩ ሰነዶች እዛና እዚህ ያሉትን፣ አካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ ህጎችን ጠቅልሎ ይዟል የተባለለት "ሁሉን አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ህግ እንዳይወጣ ፕሮጀክት እየቀረጹ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ "መነገጃ"የሚያደርጉ አሉ ተባለ፡፡
በሌላ በኩል ሁሉን አቀፍ ህጉ እንዲፀድቅ አካል ጉዳተኞች ጠይቀዋል፡፡
በተለያየ ቦታ ተበጣጥሶ የሚገኘውን እና ለመተግበርም አመቺ ያልሆኑትን አካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ ህጎች በአንድ ወጥ ፖሊሲ እንዲወጣ ታምኖበት ስራው ከተጀመረ ዓመታት እያለፉ ነው፡፡
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚለው ሁሉን አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲ ተሰናድቶ ለፍትህ ሚኒስቴር የተላከው ባለፈው ዓመት ሐምሌ 2/2015 ዓ.ም ነው፡፡
የፍትህ ሚኒስቴር ረቂቁ ከተመለከተ በኋላ አቀራረፁ ጉድለት አለበት፣ ከህግ ይልቅ ኮንቬንሽን ይመስላል በሚል በየአንቀፆቹ አስተያየት ከመስጠት ይልቅ ጥቅል አስተያየቱን በጥቅምት ወር 2016 ለሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰጥቷል፡፡
በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ወሪ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ አሳልፈው አህመዲን እንደ ሚሉት የፍትህ ሚኒስቴር የሰጠው ጥቅል አስተያየት ስለሆነ ረቂቅ ፖሊሲው ጉድለቱ ምንድነው እንነጋገርበት በሚል በህዳር ወር 2016 ዓ.ም ደብዳቤ ብናስገባም እስካሁን መልስ አላገኘንም ብለዋል፡፡
ሁሉን አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ህግ ህግ ሆኖ እንዳይፀድቅ በረቂቅ ህጉን ተጠቅመው ፣ ለግንዛቤ ስራ ፣ አድቮኬሲ እያሉ ጥቅም ማግኛ ያደረጉት አሉ ሲሉ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ አሳልፈው አህመዲን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማያውቃቸው መድረኮችም እየተዘጋጁ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ህጉ እንዲፀድቅ አልገፋበትም ፣ ለውይይት በሩን እንዲከፍት ቢጠየቅም መልስ አልሰጠም በሚል ስሙ የተነሳውን የፍትህ ሚኒስቴርን መልስ በዚህ ዘገባ ለማካተት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡
ንጋቱ ሙሉ
Comentarios