ነሐሴ 6፣2016 -''መንግሥት የሕወሐትን የሕግ ሰውነት ጉዳይ በተመለከተ በፕሪቶሪያ ስምምነት ውስጥ የወሰደው ግዴታ'' የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
- sheger1021fm
- Aug 12, 2024
- 2 min read
''የፌዴራል መንግሥት የሕወሐትን የሕግ ሰውነት እና የምዝገባ ጉዳይ በተመለከተ በፕሪቶሪያ ስምምነት ውስጥ የወሰደው የተለየ ኃላፊነት ወይም ግዴታ አልነበረም ትርጉም አልባ ንትርክንም እናስወግድ'' ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ተናገረ።
አግልግሎት መ/ቤቱ የፕሪቶሪያ ስምምነት መነሻና መድረሻው ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን ማክበር ነው በሚል ርዕስ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ “አላስፈላጊ እና ሕዝብን የማይጠቅም፣ ትርጉም አልባ ንትርክን አስወግደን ለሕዝብ ረብ ያላቸው ጉልህ የሰላም እና የልማት አጀንዳዎች ላይ ልናተኩር ይገባል” ብሏል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈጸም የፌዴራል መንግሥት በስምምነቱ የገባው ግዴታ የሕወሓት የሽብርተኝነት ፍረጃ እንዲነሣ ሂደቱን የማሣለጥ ኃላፊነት እንጂ የፓርቲው ህጋዊ ሰውነት የመመለስ ኃላፊነት አይደለም ሲል መግለጫ አስረድቷል፡፡
ሰሞኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፍትሕ ሚኒስቴር የሰጠውን ማረጋገጫ እና ህወሓት ያቀረባቸውን ሠነዶች መሠረት በማድረግ ህወሓት በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
መንግስት በዚህ በኩል ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ከህወሓት አመራሮች ጋር ተደጋጋሚ ምክክሮችን በማድረግ ፓረቲው እንደ ፖለቲካ ፖርቲ ሕጋዊ ዕውቅና እንዲኖረው ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሷል፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን የምርጫ አዋጅ ተሻሽሎ የትጥቅ እንቅስቃሴ ላይ ያሉ ቡድኖች ወደ ሕጋዊ መሥመር ሊመጡ የሚችሉበትን መንገድ የሚያመቻች የሕግ ማሻሻያ መደረጉን በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
በዚህም መሰረት የሕወሐት ሕጋዊ ሰውነት ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ተደርጓል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ተናግሯል፡፡
በተደረገው የሕግ ማሻሻያ መሠረት ምርጫ ቦርድ ህወሃትን በመመዝገብ ድርጅቱ ሕጋዊ ሰውነት እና ዕውቅና እንዲኖረው የፍትህ ሚኒስቴር ለቦርዱ የትብብር ጥያቄ አቅርቧል ተብሏል።
ይህንንም ተከትሎ ህወሓት ሕጋዊ ሰውነት እና ዕውቅና ለማግኘት የሚጠበቅበት የፓርቲ ሰነዶቹን ማለትም የፓርቲውን ፕሮግራም እና ሕገ ደንብ፣ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ሰነዶችን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማቅረብ በተሻሻለው አዋጅ መሠረት ተመዝግቦ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቷል ሲል አስረድቷል፡፡
ስለሆነም የምዝገባ እና የህግ ሰውነትን ጉዳይ በዚህ በመቋጨት፤ የሁሉም ባለድርሻ አካል ርብርብ፣ ሰላምን በማጽናት፣ በመልሶ ግንባታ እና በልማት አጀንዳ ላይ ሊሆን ይገባል ሲል አገልግሎቱ አሳስቧል።
አላስፈላጊ እና ሕዝብን የማይጠቅም፣ ትርጉም አልባ ንትርክን አስወግደን ለሕዝብ ረብ ያላቸው ጉልህ የሰላም እና የልማት አጀንዳዎች ላይ ልናተኩር ይገባል ሲልም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ተናግሯል።
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments