ነሐሴ 5፣2015 - የውሃ የዲፕሎማሲ እና የኮሚኒኬሽን ስራን ዩኒቨርሲቲዎች ሊመሩት ይገባል ተብሏል
- sheger1021fm
- Aug 11, 2023
- 1 min read
ከውሃ ጋር የተገናኘ የኮሚኒኬሽን እና የዲፕሎማሲ ስራን ምሁራን ተሰባስበው በሳይንሳዊ መንገድ መምራት ስላልቻሉ ኢትዮጵያ በአለም መድረክ ተጎጂ ሆናለች ተባለ፡፡
የውሃ የዲፕሎማሲ እና የኮሚኒኬሽን ስራን ዩኒቨርሲቲዎች ሊመሩት ይገባልም ተብሏል፡፡
ዘጠነኛው የውሃ፣ ዲፕሎማሲ እና የኮሚኒኬሽን ጉባኤ ዛሬ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተጀምሯል፡፡
በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ እንዳሉት ለዘመናት ከውሃ ዲፕሎማሲ ጋር የተገናኘው ስራ በመንግስት እጅ ብቻ ተይዞ ስለቆየ ሀሳቡ ፖለቲካዊ ብቻ ተደርጎ ይወሰድ ነበር፡፡
ከውሃ ጋር የተገናኘውን ስራ ሳይንሳዊ ማድረግ የሚቀርብበትን መንገድም እንደአስፈላጊነቱ በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲሆን ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ያሉ ባለሞያዎችን ማሰባሰብ ባለመቻሉ ኢትዮጵያ በአለም ፊት በተደጋጋሚ የበታች ሆና ታይታለች ብለዋል፡፡
በህዳሴው ግድብና በሌሎችም ውሃ ነክ ፕሮጀክቶች በአለም መድረክ ኢትዮጵያ ያላትን እውነት ከማስረዳት ይልቅ እነ ግብፅ ከሳሽ እሷ ደግሞ ተከሳሽ ሆና እንድትታይ አድርጓታል ተብሏል፡፡
ይህንን ለመቀየር በማሰብም የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ምዑራን በውሃ ዲፕሎማሲና ኮሚኒኬሽን ስራ እንዲሰባሰቡ በማሰብ ከሁለት ዓመት በፊት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው የውሃ ጉባኤ ተካሂዷል፡፡
በጉባኤው በባለሞያዎች የሚቀርቡ ውሃን የተመለከቱ ጥናታዊ ፅሁፎች በእንግሊዘኛና በአረብኛ ቋንቋዎች እየታተሙ ለአለም እንዲቀርቡ የማድረግ ስራ ይሰራል ተብሏል፡፡
የመጀመሪያው የእንግሊዘኛው እትምም በቅርቡ ይፋ ተደርጓል፡፡
ዛሬ ሙሉ ቀን በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተካሄደ ባለው 9ኛው የውሃ ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሚኒኬሽን ጉባኤ ላይ 4 ጥናታዊ ፅሁፎች ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ላይ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት በግንባታ ሂደት ላይ ያለው በውሃ ዙሪያ የሚሰሩ ጥናታዊ ፅሁፎችን በቀላሉ ማግኘት እና መሰነድ የሚቻልበት ዲጂታል የኢግዚቢሽን ማዕከልና የመረጃ ማዕከል ወይም ዳታ ሴንተር ግንባታ ተጎብኝቷል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የበላይ ሆኖ የሚመራው ከውሃ ጋር የተገናኘ የጥናት እና ምርምር ስራን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመምራት የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል፡፡
የመግባቢያ ሰነዱን ከውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር የተፈራረሙት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የአርባ ምንጭ፣ የባህር ዳርና የጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው፡፡
በስብስቡ ውስጥ በሂደት ሌሎች ዩኒቨርስቲዎችም ይካተታሉ ተብሏል፡፡
ቴዎድሮስ ወርቁ

የሸገርንወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Commentaires