top of page

ነሐሴ 4፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች

 

አብዮታዊ ዘብ የተሰኘው የኢራን የጦር ክፍል እስራኤል እንድትቀጣ የአገሪቱ መንፈሳዊ መሪ የሰጡት ትዕዛዝ ተፈፃሚ ይሆናል አለ፡፡

 

የቀድሞው የሐማስ መሪ ኢስማኤል ሐኒያ ባለፈው ሳምንት በቴሕራን ከተገደሉ በኋላ ኢራን ለዚህ ወንጀል ከእስራኤል ራስ አልወርድም እያለች ነው፡፡

 

እስራኤል ሐኒያን አስገድላቸዋለች ለመባሉ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠችም፡፡

 

የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ ዓሊ ሐሚኒ የሐኒያን ደም ለመበቀል እስራኤልን ቅጡልኝ ካሉ ሰንብተዋል፡፡

 

አብዮታዊ ዘብ የተሰኘው የኢራን የጦር ክፍል መሪያችን ለብቀላው የሰጡት ትዕዛዝ ተፈፃሚ ይሆናል ማለቱን አልጀዚራ ፅፏል፡፡

 

ይህም በእስራኤል እና በኢራን መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩን ዘገባው አስታውሷል፡፡

 

የሞዛምቢክ የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስቴር ማኑኤል ቻንግ በከፍተኛ ማጭበርበር እና ምዝበራ በአሜሪካ ፌዴራል ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተባሉ፡፡

 

ማኑኤል ቻንግ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባሉት የሞዛምቢክ የገንዘብ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በህገ ወጥ መንገድ ከተወሰደ የ2 ቢሊዮን ዶላር ብድር ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች እንደሆነ ዩሪስት ኒውስ ፅፏል፡፡

 

ይሄ የብድር ውጥንቅጥ ሞዛምቢክ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር የነበራትን ግንኙነት አበላሽቶ መቆየቱን ዘገባው አስታውሷል፡፡

 

የብድር ገንዘብ ባክኖ መቅረቱ ይነገራል፡፡

 

ማኑኤል ቻንግ በዚሁ ምክንያት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተያዙት ከ6 ዓመታት በፊት ነው፡፡

 

ሞዛምቢክም እፈልጋቸዋለሁ ብትልም ደቡብ አፍሪካ ለአሜሪካ አሳልፋ ሰጥታቸዋለች፡፡

 

ማኑኤል ቻንግ ጥፋተኛ በተባሉበት ጉዳይ አስከ 20 አመታት የሚዘልቅ እስር ሊፈረድባቸው ይችላል፡፡

 

 

በብራዚል አንድ የመንገደኞች ማጓጓዣ አውሮፕላን በመውደቁ የ61 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰማ፡፡

 

አደጋው የደረሰው በሳኦ ፓውሎ ግዛት እንደሆነ ሚንት ፅፏል፡፡

 

አውሮፕላኑ ሰራተኞቹን ጨምሮ 61 ሰዎችን አሳፍሮ ነበር ተብሏል፡፡

 

አንድም በሕይወት ተራፊ እንዳልተገኘ ታውቋል፡፡

 

አውሮፕላኑ በአንድ የመኖሪያ አካባቢ መውደቁ ተሰምቷል፡፡

 

በአደጋው በአንድ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡

 

አውሮፕላኑ በምን ምክንያት ሊወድቅ እንደቻለ ለጊዜው የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡

 

ፕሬዘዳንት ሉላ ኢናሲዮ ዴ ሲልቫ በአደጋው ከልቤ አዝኛለሁ ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

 

ኮንጎ ኪንሻሣ

 

በኮንጎ ኪንሻሣ መንግስትን በሀይል ለመጣል ከአማጺያን ጋር ተመሳጥረዋል የተባሉ 26 ሰዎች በሞት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው፡፡

 

በግለሰቦቹ ላይ የሞት ቅጣት ውሳኔው የተላለፈባቸቸው በጦር ፍርድ ቤት እንደሆነ ቢዝነስ ዴይሊ ፅፏል፡፡

 

የሞት ፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው ግለሰቦች ከM-23 እና ከሌሎች አማጺ ቡድኖች ጋር ሲተባበሩ ቆይተዋል ተብሏል፡፡

 

በሞት እንዲቀጡ ከተፈረደባቸው መካከል የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን የቀድሞ የበላይ ኮርኔል ናንጋም እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡

 

ፍርደኞቹ ቀደም ሲል መንግስትን በሀይል ለመጣል AFC የተሰኘ ጥምረት ማቋቋማቸው እንደተደረሰበት ተጠቅሷል፡፡

ናንጋ እና ሌሎች 20 ተከሳሾች የሞት ፍርድ ውሳኔው የተላለፈባቸው በሌሉበት መሆኑ ታውቋል፡፡

 

የኔነህ ከበደ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page