top of page

ነሐሴ 4፣2016 - ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገብ የሚያስችለውን ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሰጠው።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገብ የሚያስችለውን ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሰጠው።


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህውሃት) የሕግ ሰውነት ጉዳይን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።


በመግለጫውም ህጋዊ ሰውነቱ ተነጥቆ የቆየው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ''በልዩ ሁኔታ'' እንዲመዘገብ መወሰኑን ተናግሯል።


ቦርዱ ለፓርቲው በልዩ ሁኔታ መዝግቦ የማረጋገጫ ወረቀት የሰጠው ትናንት  ነሐሴ 3፣2016 ዓ.ም እንደሆነ ምርጫ ቦርድ ከፃፈው ደብዳቤ ላይ ተመልክተናል።


ህወሃት በአመጻ ተግባር ተሳትፎአል በሚል ከህጋዊ ፓርቲነቱ በምርጫ ቦርድ ተሰርዞ ቆይቶ እንደነበረ የሚታወቅ ነው።


አሁን ምርጫ ቦርድ ለፓርቲው  እውቅና የሰጠው በቅርብ የተሻሻለው፤ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች መዝገባና ምርጫ  ስነምግባር አዋጅ  1332/2016 አንቀጽ 2 መሰረት እንደሆነ ተናግሯል።


ሕወሃት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ህጋዊ ሰውነቱ ዳግም እንዲመለስለት ሲጠይቅ መቆየቱ ይታወቃል።


ነገር ግን ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011ን ያሻሻለው ዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 በዓመፅ ተግባር ተሠማርቶ ለተሠረዘ ፓርቲ የቀድሞውን ኅልውና መልሶ የሚሰጥ የሕግ ድንጋጌ አልያዘም ብሏል ቦርዱ።


በመሆኑ ቦርዱ የቀረበለትን የህውሀትን ሕጋዊ ሰውነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ የሚለውን ጥያቄ አልተቀበልኩትም ብሏል፡፡


ነገር ግን የፍትሕ ሚኒስቴር በማሻሻያ ዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀጽ 2 (1) መሠረት ሰኔ 17/2016 በቁጥር ፍሚ1/1345 ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ ህ.ወ.ሓ.ት ኃይልን መሠረት ያደረገ የዐመፅ ተግባሩን በማቆም ሕገ-መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ የተስማማ መሆኑን ተጠቅሷል።

ይህም በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ማሻሻያ ዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀፅ 2 (1) መሠረት ''በልዩ ሁኔታ'' እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ የሚያስችለው ነው ብሏል።


በመሆኑም የፍትሕ ሚኒስቴር የሰጠውን ማረጋገጫ እና ህ.ወ.ሓ.ት ያቀረባቸውን ሠነዶች መሠረት በማድረግ ህ.ወ.ሓ.ት በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ ቦርዱ እንደወሰነ አስረድቷል፡፡

 

ፓርቲው ''በልዩ ሁኔታ'' የመመዝገብ ውሣኔን የያዘው ደብዳቤ ከደረሰው ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራቶች ውስጥ፣ የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርግ፤ በዚህ ጉባዔም መተዳደሪያ ደንቡን እንዲያፀድቅ፣ አመራሮቹን እንዲያስመርጥ ቦርዱ መወሰኑ ተሰምቷል፡፡

 

ጠቅላላ ጉባዔው በቦርዱ ከፀደቀ በኋላ ባሉት የአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ውስጥ ፓርቲው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆን አለመሆኑ በዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀጽ 3 መሠረት ቦርዱ ክትትል ያደርጋል ተብሏል።


ማንያዘዋል ጌታሁን

Comments


bottom of page