top of page

ነሐሴ 30፣2016 - ኢትዮጵያ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመስራት 1.6 ቢሊዮን ዶላር ብታወጣም ባለፉት 9 ዓመታት ከፓርኮቹ ያገኘችው ገቢ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡

ኢትዮጵያ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመስራት 1.6 ቢሊዮን ዶላር ብታወጣም ባለፉት 9 ዓመታት ከፓርኮቹ ያገኘችው ገቢ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡


ይህ የተባለው ዛሬ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እና ከኢንዱስትሪ አልሚዎች ጋር እየመከረ ባለበት ወቅት ነው፡፡


ኢትዮጵያ ከ9 ዓመት በፊት ወደ ስራ የገቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማልማት ኢትዮጵያ 1.6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ አውጥታለች ተብሏል፡፡


ይሁንና እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ባለፉት 9 አመታት ለኢትዮጵያ ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ ልከው ለኢትዮጵያ ያስገቡት ዶላር ከ1.2 ቢሊየን ዶላር ያልዘለለ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዋና ዳይሬክተር ፍሰሐ ይታገሱ(ዶ/ር ) ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በስራ ላይ ያሉ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች 85 በመቶ የሚሆነው ሼዶቻቸው ተይዟል የተባለ ሲሆን 15 በመቶ ደግሞ አልሚዎችን የሚጠብቁ ናቸው ብለዋል፡፡


እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች 70,000 ሺህ ለሚሆኑ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠራቸውንም ዶ/ር ፍሰሐ አስረድተዋል፡፡


በተለያዩ ምክንያቶች ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የወጡ አልሚዎች መሆናቸውንም ዋና ስራ አስፈፃሚው አስረድተዋል፡፡


የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ ችግሮችን በተመለከተ መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት ዶ/ር ፍሰሐ የውጪ ምንዛሪ እጥረት በቂ ጥሬ እቃ ወይንም ግብአት አለመገኘት እና የሀገር ውስጥ ግጭቶችና አለም አቀፍ ተፅዕኖዎች እንቅፋት ሆነው በመንግስት በኩል የቆዩ ችግሮች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡


ይህንንም ለመፍታት መንግስት በቅርቡ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ያስረዳል ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚነሱ የመብራት፣ የውሃ እና መንገድ መሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ እንዳለ ተናግረዋል፡፡


ባለፉት 6 ዓመታትም የመንገድ፣ የሀይልና የሎጅስቲክስ አገልግሎቱ ተሻሽሏል ብለዋል፡፡


በዚህም የኢንዱስትሪ ፓርኮች 24,000 ኪሎ ሜትር መንገድ ተዘርግቷል ያሉ ሲሆን በሚመጡት 10 አመታት የመንገድ ተደራሽነትን 245,000 ኪሎ ሜትር ለማድረስ አቅደናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡


ያሬድ እንዳሻው


Comments


bottom of page