አሁን የሚታዩ ግጭቶችን ማስቆም ካልተቻለ የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ ለማድረግ አዳጋች ይሆናል ተብሏል፡፡
የሽግግር ፍትህ የባለሞያዎች ቡድን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ሊደረግ ስለታሰበው የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ ማዕቀፍ ለማሰናዳት የሚያግዙ አማራጮች ላይ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
የባለሞያዎች ቡድኑ ዛሬ በፍትህ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ ስለ ሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አማራጮች በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት በማድረግ ምክረ ሀሳቦችን ሲያሰባስብ መቆየቱን የባለሞዎች ቡድኑ ተናግሯል፡፡
በሂደቱ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የምክክር መድረኮችን በተፈለገው መጠን ለማካሄድ ተቸግረው እንደነበር አንስተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በደንቢ ዶሎ እና ያቤሎ ከተሞች ውይይት ለማድረግ እንዳልተቻለ ሰምተናል፡፡
በአማራ ክልልም ውይይት ለማካሄድ የተያዙ መርሐ ግብሮች በተደጋጋሚ ለማጠፍና ለመቀየር የተገደዱባቸው አካባቢዎች እንደነበሩ በመግለጫቸው አክለዋል፡፡
ይሁንና የፖሊሲ ማዕቀፍን ለማዘጋጀት የሰላም እጦቱ ያን ያህል ጉልህ ተፅዕኖ አሳድሯል ባይባልም የሽግግር ፍትህ ተግባራዊ ለማድረግ ግን የግድ ሰላም ማስፈን ስለሚያስፈልግ የሚመለከታቸው ሁሉ ለሰላም እንዲሰሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የፖሊሲ ማዕቀፉን አማራጭ በተመለከተ ህብረተሰቡ ያለውን ሀሳብ እንዲያዋጣ ከ50 በላይ መድረኮች ተዘጋጅተው ውይይት ተደርጓል ተብሏል፡፡
በሂደቱም 200 የዩኒቨርስቲ መምህራንም ተሳታፊ እንደነበሩ የባለሞያዎች ቡድኑ ተናግሯል፡፡
እንደማሳያ በአዲስ አበባ በተካሄደው ምክክር ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ በቀይ ሽብር ወቅት ለተፈፀሙ ወንጀሎች ፍትህ ለመስጠት የተሳተፉ ዳኞችና ዐቃቢያነ ህጎችን ያሳተፉ እንደነበሩ ሰምተናል፡፡
ዝርዝር ውይይት ተደርጎ ስለ እውነትን ማፈላለግ፣ እርቅን ስለማስፈን እና ተጠያቂነትን ለማምጣት ያግዛል ለተባለው ለሽግግር ፍትህ የፖሊሲ ማዕቀፍ ሀሳብ አዋጥተዋል ሲል ቡድኑ አስረድቷል፡፡
በመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት በአዲስ አበባ የተወሰኑ የውይይት መድረኮችን በማከል ዋና ዋና ግኝቶችን በማደራጀት ረቂቅ የሽግግር ፖሊሲ ማዕቀፍ ተሰናድቶ ለመንግስት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments