top of page

ነሐሴ 3፣2016 - በይርጋለም ማረሚያ ቤት ለ60 ሰው ተብሎ በተገነቡ ክፍሎች 240 ታራሚዎች ተፋፍገው እንደሚኖሩበት ተነገረ

በይርጋለም ማረሚያ ቤት ለ60 ሰው ተብሎ በተገነቡ ክፍሎች 240 ታራሚዎች ተፋፍገው እንደሚኖሩበት ተነገረ፡፡


በ1945 ዓ.ም ተገንብቶ ላለፉት ለ80 ዓመታት ገደማ ምንም ዓይነት ማሻሻያ ሳይደረግበት በቀጠለው በዚህ ማረሚያ ቤት ታራሚዎች ለተላላፊ በሽታዎች ጭምር እየተጋለጡ መሆኑን ሰምተናል፡፡


በአጠቃላይ 800 ታራሚዎችን ይይዛል ተብሎ የተሰራው ይህ ማረሚያ ቤት በአሁኑ ሰዓት 4,000 ገደማ ታራሚዎችን እንደያዘ ሴንተር ፎር ጀስቲስ የተባለውና በጉዳዩ ላይ የሚሰራው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተናግሯል፡፡


በጊዜው ለ60 ታራሚዎች ተብለው የተገነቡት ክፍሎችም አሁን 240 ታራሚዎች እያስተናገዱ በመሆኑ ታራሚዎቹ ለተለያዩ ችግሮች እንደተጋለጡ ሰምተናል፡፡


ይርጋለምን ጨምሮ በተለይም በክልሎች ያሉ ማረሚያ ቤቶች፤ ሲገነቡ ታሳቢ ከተደረገላቸው ታራሚ ቁጥር በላይ እያስተናገዱ ነው መባሉንም ሰምተናል፡፡


ይህንን በማረሚያ ቤቶቹ ላይ ባደረኩት ተደጋጋሚ ጥናት አረጋግጫለሁ ብሏል ሴንተር ፎር ጀስቲስ፡፡


ታራሚዎች እጅግ በተጨናነቀ ክፍሎች መሆናቸው ለተለያዩ ችግሮች እየተዳረጉ መሆኑን የሴንተር ፎር ጀስቲስ ድርጅት ዳይሬክተር ኩምሳ ጉተታ ነግረውናል፡፡

ለተላላፊ በሽታዎች መጋለጥ ታራሚዎቹ ከሚደርሰባቸው ችግሮች አንዱ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡


የወንጀል ፈጻሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት፣ በማረሚያ ቤቶች ላይ ማሻሻያ አለመደረጉ፣ የአማራጭ ቅጣጦች ተግባራዊ አለመደረጋቸው፤ በማረሚያ ቤቶቹ ለሚታየው መጨናነቅ በጥናቱ ከተለዩት ዋነኛ ምክንያቶች መካከል ናቸው ሲሉም አቶ ኩምሳ አስረድተዋል፡፡


የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ በማረሚያ ቤቶች ላይ እስረኞች በተጨናነቀ ክፍሎች እንደሚስተናገዱ አልሸሸጉም፡፡

ለዚህ መጨናነቅ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ማረሚያ ቤቶቹ የሀብት እጥረት ስላለባቸው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡


በተለይ በክልል ማረሚያ ቤቶች ያለውን የማረሚያ ቤቶች መጣበብን ለመቀነስ ከክልሎች ጋር በመነጋገርና ድጋፍም ለማድረግ ውጥን መያዙን ኮሚሽነሩ ተናግሯል፡፡


ማንያዘዋል ጌታሁን ያሰናዳውን በትዕግስት ዘሪሁን


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page