top of page

ነሐሴ 29፣2016 - በዓሉን ምክንያት አድርገው ምርት የሚያሸሹና የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን እንደማይታገስ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ተናገረ

በዓሉን ምክንያት አድርገው ምርት የሚያሸሹና የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን እንደማይታገስ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ተናገረ፡፡


ከፊታችን ለሚከበረው የአዲስ ዓመት በዓል ለሸማቹ የሚያስፈልጉ የሁሉም ዓይነት ሸቀጦች በቂ አቅርቦት እንዳለ ቢሮው ለሸገር ራዲዮ ተናግሯል፡፡


በመሆኑም ዋጋ ሊያስጨምር የሚችል የአቅርቦት እጥረት ስለማይኖር ያለ አግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን አልታገስም ብሏል፡፡


ለዚህ ሲባል በተቋቋመው ግብረ ሀይል አማካኝነት እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል።


ከዚህ ቀደምም በህገ-ወጥ ንግድ ላይ ተሰማርተዋል የተባሉ ከ1,600 በላይ ነጋዴዎች የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውና ከ600 በላዩ ሱቃቸው እንደታሸገባቸው የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ነግረውናል፡፡


ለበዓሉ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በበቂ መጠንና በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓልም ብሏል፡፡


በመዲናዋ በተገነቡ የንግድ ማዕከላት ባዛሮች መዘጋጀታቸውንና በ193 የሰንበት ግብይት ቦታዎች ለ10 ተከታታይ ቀናት ምርቶች እየቀረቡ መሆኑን የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ሰውነት ጠቅሰዋል።

ይሁንና ወቅቱ ክረምት እንደመሆኑ በከተማዋ የቀይ ሽንኩርት እጥረት መኖሩን የጠቀሱት ሃላፊው ይህንን እጥረት ለመቅረፍ ለበዓሉ 500,000 ኩንታል፣ ቲማቲም 30,000 ኩንታል፣ ጤፍ 22,000 ኩንታል፣ ዘይት ከ3 ሚሊዮን ሊትር በላይ፣ ስኳር 16,000 ኩንታል፣ዱቄት 17,000 ኩንታል እንዲሁም ሌላውም እየቀረበ ነው ብለዋል፡፡


በተጨማሪም በዓሉን ተከትሎ ለእርድ የሚፈለጉ እንሰሳት እጥረት እንዳይኖር ከኢትዮጵያ የቁም እንሰሳት ማህበር ጋር በመሆን 20,000 በግና ፍየል፣ ከ62,000 በላይ በሬ፣ ከዶር አርቢዎች ጋር በመሆንም ከ282,000 በላይ ዶሮ ወደ ከተማ እየገባ መሆኑን አስረድተዋል፡፡


ከሁሉም ዓይነት በቂ ምርት ወደ አዲስ አበባ እየገባ በመሆኑ ምንም ዓይነት የምርት እጥረት እንደማይኖር ከሃላፊው ሰምተናል፡፡


ዋጋን ያለ አግባብ ሲጨምሩ የተመለከታችኋቸው ነጋዴዎች ካሉ በ8588 ነፃ መስመር ጠቁሙን ተብላችዋል፡፡



ምንታምር ፀጋው

Comments


bottom of page