ንፁሐን ዜጎችን በማገት፣ ገንዘብ በመቀበልና በመግደል ተሳትፎ አላቸው የተባሉ የመንግስት መዋቅር አባላት ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ተናገረ፡፡
ከሰሞኑ በተለይ በጎነደር አካባቢ የህዝብን ቁጣ የቀሰቀሰ ተደጋጋሚ እና አሰቃቂ የእገታ ወንጀሎች መፈጸማቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ ቆይቷል፡፡
በዚሁ ጉዳይ ትናንት ማምሻውን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ባወጣው መግለጫ የመንግስት አካላት ሆነው ሃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ የችግሩ አባሪና ተባባሪ በመሆን ህዝብን እየበደሉ ያሉትን አካላት ላይ የተጠናከረ ርምጃ መውሰድ ተጀምሯል ብሏል፡፡ እስካሁንም የዚህ ድርጊት ተባባሪ ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩ 14 የፀጥታ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራ መሆኑን አሳውቋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የክልሉ መንግስት በጎንደር ቀጠና በሚገኙ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ላይ የሚገኙ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት የተሳናቸው የአቅምም ሆነ የስነ ምግባር ችግር ያለባቸውን ሃላፊዎች በየደረጃው ከሃላፊነት በማንሳት ተጠያቂ ለማድረግ የተጀመረ የኦፕሬሽን ስራም መኖሩን የጠቀሰው መግለጫው ይህም በርትቶ ይቀጥላል ሲል አክሏል፡፡
በአማራ ክልል የዘረፋ፣የእገታና ግድያ ወንጀሉ የሚመራው በታጣቂው ቡድን መሆኑን የሚያረጋግጡ መረጃና ማስረጃዎችም አሉኝ ብሏል ቢሮው፡፡ በመሆኑም የፀጥታ መዋቅሩ የኦፕሬሽን እቅድ አዘጋጅቶ አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰደ ይገኛል ሲልም ተናግሯል፡፡ ሰሞኑን በተከታታይ በጎንደር ከተማ ለተከሰተው እገታ እና ግድያም የክልሉ መንግስት ሃላፊንቱን ለታጣቂው ቡድን ሠጥቷል፡፡
ሆኖም ግን መንግስትና የመንግስት የፀጥታ መዋቅር ድርጊቱ እንዲታረምና የህዝብ እንባ እንዲቆም ለማድረግ የህይወት መሰዋትነት ጭምር እየከፈሉ እየታገሉ ባሉበት ሁኔታ ይህን ዋጋ በሚያሳጣ መንገድ እና እውነቱን በማድበስበስ ችግሩን ለመንግስት አካል ጠቅልሎ በመስጠት አጥፊውን ሃይል ነፃ ለማድረግ የተሞከረበት ፐሮፓጋንዳ ስለመኖሩም በመንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ማምሻውን የተሰራጨው የቢሮው መግለጫ ያትታል፡፡
ህዝቡ ከመንግስት ጋር በመተባበር ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ ሲገባ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ባላቸው ሃይሎች ያልተገባ ቅስቀሳና የአመፅ ጥሪ፣ የተሸከርካሪ ገደብ፣ የስራ እንቅስቃሴን ማስተጓጎልና የዜጎችን ህይወት በማጎሳቆል ህዝቡን ለከፋ የኑሮ ውድነትና ተጨማሪ ቀውስ መዳረግ ውጤት አልባ በመሆኑ ህዝቡ እንዳይሳተፍ እና በንቃት እንዲታገለው የሰላም እና የጸጥታ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል፡፡
የድርጊቱን ፈጻሚዎችን እና ከዚህ ጉዳይ ጋር ትስስር ያላቸውን አካላት ተጨማሪ ጥብቅ ማጣራት ካደረገ በኋላ የማያዳግም እርምጃ ወስዶ ለህዝብ አሳውቃለሁ ሲልም የክልሉ መንግስት ቃል ገብቷል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
Komentarze