በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ እገታዎች ተባብሰውና ተስፋፍተው መቀጠላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) የክትትልና ምርመራ ውጤት አሳየ፡፡
እገታቸውቹ የሚፈጸሙትም በታጣቂ ኃይሎች፣ ለዘረፋ በተደራጁ ቡድኖች እንዲሁም በአንዳንድ የመንግሥት የጸጥታ አካላት አባሎች መሆኑን ኢሰማኮ አስረድቷል፡፡
በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከተራዘሙ የትጥቅ ግጭቶች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የሕግ ማስከበር እና የመንግሥት መዋቅር መላላት ሳቢያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ እገታዎች መቀጠላቸውን ኮሚሽኑ ጠቅሷል፡፡
አጋቾች ሰላማዊ ሰዎችን በአብዛኛው በጉዞ (ትራንስፖርት) ላይ እያሉ አንዳንዴም ከመኖሪያ ቤታቸው ወይም ከሥራ ቦታቸው አግተው ወዳልታወቀ ቦታ በመውሰድ ከፍተኛ የማስለቀቂያ ገንዘብ ክፍያ ይጠይቃሉ።
ገንዘብ መክፈል ያልቻሉ በርካታ ታጋቾች ግድያን ጨምሮ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈጽሞባቸዋል ሲል የኮሚሽኑ የክትትልና ምርመራ ውጤት አሳይቷል ።
እገታው በአብዛኛው እንደ ገቢ ማስገኛ የተወሰደ መሆኑን፤ በተደጋጋሚ፣ በተንሰራፋና በተደራጀ መልኩ እንደሚፈጸም፤ አልፎ አልፎም እንደ በቀል፣ ለፖለቲካ ዓላማ ወይም የታገተ ሌላ ሰውን ለማስለቀቅ በሚል በአጸፋ መልኩ የሚፈጸም መሆኑን ተረድቻለሁ ብሏል፡፡
ይህም በሲቪል ሰዎች መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶች በተለይም በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት፣ የንብረት መብት እና የመዘዋወር ነጻነት ላይ ጥሰት የሚያደርስ እንዲሁም በታጋቾችና ቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የሚያስከትል እና ለተራዘመ ጊዜ በፍርሃት እና በሥጋት ውስጥ እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው ሲል ኮሚሽኑ ተናግሯል።
በተጨማሪ ታጋች ሴቶች ለአስገድዶ መደፈር እና ለተለያየ ጾታዊ ጥቃት ይዳረጋሉ፣ በማኅበረሰቡ ደኅንነት እና ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች እንዲሁም በሕግ የበላይነት መከበር ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖም ከፍ ያለ ነው ተብሏል።
ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደታየው በዚህ ዐይነት መንገድ የሚገኝ ገንዘብ ለመሣሪያ ግዢ ሊውል የሚችል ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ግጭቶቹን ሊያራዝም እንዲሁም ግጭቶቹን በዘላቂነት ለማስቆም በሚደረገው ድርድር ችግሮች ሊሆን ይችላል ሲል ስጋቱን ጠቅሷል።
ኢሰመኮ በዚህ መግለጫው የእገታ ጉዳዮች ለማሳያነት አቅርቧል፡፡
በዓለም አቀፉ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ማዕቀፎች መሠረት ሰዎች የነጻነት፣ አካላዊ ደኅንነት፣ ከጭካኔ እና ኢ-ሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ እና በሕይወት የመኖር መብቶች በመንግሥት አካላት ብቻ ሳይሆን በሦስተኛ ወገኖች ወይም ድርጅቶች ጭምር እንዳይጣሱ በሚገባ መከላከል አለባቸው። ለዚህም አስፈላጊውን የመከላከል እና የጥበቃ እርምጃ ሁሉ መውሰድ የሚገባቸው ሲሆን፣ ጥሰቶች ሲፈጸሙም ተገቢውን ምርመራ በማድረግ የአጥፊዎችን ተጠያቂነት እና የተጎጂዎችን ተገቢውን ፍትሕ የማግኘት መብት ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።
በተጨማሪም፣ በጦርነት ዐውድ ውስጥ የሚፈጸም እገታ በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት እንዲሁም የወንጀል ሕግ መሠረት የጦር ወንጀልን ሊያቋቁም የሚችል በመሆኑ፣ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የታጠቁ ቡድኖችም ድርጊቱን ከመፈጸም የመታቀብ ዓለም አቀፍ ግዴታ አለባቸው ሲል አስስቧል።
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች መሠረት ማንኛውም ሰው የተሟላ ነጻነትና ደኅንነት የማግኘት መብት እንዳለው እና ይህንንም ነጻነት በዘፈቀደ ሊነፈግ እንደማይገባ አስታውሰዋል።
“በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች አሳሳቢ ሆኖ ለቀጠለው የእገታ ተግባር ዘላቂ በሆነ መልኩ እልባት ለመስጠት ለሰዎች እገታ መነሻና አባባሽ ምክንያት የሆነውን የሰላም መደፍረስና የትጥቅ ግጭትን በዘላቂነት በሰላማዊ መንገድ መፍታትን ጨምሮ ውጤታማ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባል” ብለዋል።
ንጋቱ ሙሉ
Comments