ነሐሴ 27፣2016 - አአዩ ከመጭው የት/ት ዘመን ጀምሮ ከፍለው የመማር አቅም ያላቸውን ተማሪዎች እንደሚቀበል ይፋ አደረገ
- sheger1021fm
- Sep 2, 2024
- 1 min read
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመጭው የትምህርት ዘመን ጀምሮ ከፍለው የመማር አቅም ያላቸውን ተማሪዎች እንደሚቀበል ይፋ አደረገ፡፡
መንግስት ወጪያቸውን የሚሸፍንላቸው ተማሪዎችም የእድሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
ራስ ገዝ የመሆን ሂደት ላይ ያለው ዩኒቨርሲቲው ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ካመጡት መካከል የራሱን ፈተና አውጥቶ በማወዳደርም ጭምር የሚያልፉትን እንደሚቀበል ዛሬ በሰጠው መግለጫ ተናግሯል፡፡
በሌላ በኩል ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት በመስጠት አለም አቀፍ ተማሪዎችን መቀበል እንደሚጀምር የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዘዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የውጭ ዜጎቹ በመጡበት ሀገር የመግቢያና ገንዘብ እንደሚከፍሉም ጠቅሰዋል፡፡
የራስ ገዝነት ስራው አሁን በሚሄድበት መንገድ ከቀጠለ በተቀመጠለት ጊዜ የራስ ገዝነት ስራው በተሳካ መንገድ እውን ይሆናል ተብሏል።
ዩንቨርሲቲው ከቅድመ ምረቃ ባሻገር 2ኛ እና 3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ቁጥር ለማብዛት እቅድ ይዘናል ያሉት ዶክተር ሳሙኤል የዩኒቨርስቲው ራዕይ በአፍሪካ ተመራጭ የምርምር ተቋም መሆን ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም ሲባል የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ቁጥሩን ከፍ ማድረግ አቅዷል መባሉም ሰምተናል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ2017 የትምህርት ዘመን ከ4,500 እስከ 5,000 ተማሪዎችን አወዳድሮ ለመቀበል አቅም አለኝ ብሏል፡፡
በረከት አካሉ
Comments