top of page

ነሐሴ 27፣2015 - የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ልዩ አገልግሎት እና አደረጃጀት ያለው ቅርንጫፍ መክፈቱን ተናገረ



የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገሪቱ የቅርንጫፍ ባንክ አገልግሎት ታሪክ የመጀመሪያ እና ልዩ አገልግሎት እና አደረጃጀት ያለው ቅርንጫፍ መክፈቱን ተናገረ፡፡


በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ውስጥ የተከፈተው የባንኩ ልዩ ቅርንጫፍ "ዓቢይ ቅርንጫፍ" መሆኑን አስረድቷል።


ዓቢይ ቅርንጫፉ የመጪውን ጊዜ የባንክ አገልግሎት አዲስ ቅርዕ ማሳያ ነው ሲሉ የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ ተናግረዋል ።


ቅርንጫፉ በአጠቃላይ በ2,586 ስኩዌር ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን ይህም በሀገሪቱ ካሉ የባንክ ቅርንጫፎች የመጀመሪያው ሰፊ ቅርንጫፍ ያደርገዋል ተብሎለታል።


ደንበኞች ሙሉ ለሙሉ የዲጅታል አገልግሎት መስጫዎችን ተጠቅመው አገልግሎት የሚያገኙበት፤ ካለ ማንም እገዛ እራሳቸውን የሚያስተናግዱበት ቮቸር ማኔጅመንት ሥርዓት የተሰራለት ነው ተብሏል።


ዓቢይ ቅርንጫፉ በኢንተርአክቲቭ ቴለር ማሽን አገልግሎት ይሰጣል የተባለ ሲሆን ፤ ደንበኞች በቪዲዮ ግንኙነት ማካኝነት የባንክ ባለሙያዎችን አግኝተው የሚፈልጉትን አገልግሎት የሚያገኘበት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡


ደንበኞች የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት፣ ገንዘብ ወጪና ገቢ ማድረግ፣ ቼክ መመንዘር እና ሌሎች አገልግሎቶችን ካለማንም እገዛ መፈጸም እንደሚያስችላቸው ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።



በቅርንጫፉ አዲስ ሐሳብ ለሚከፍቱ ደንበኞች በዲጅታል ሥርዓት ፎቶግራፍና ፊርማ የሚቀበል መሆኑም ተነግሮለታል።


የዓቢይ ቅርንጫፉ መከፈት ባንኩ ለታላላቅ እና ኮርፖሬት ደንበኞቹ የሚሰጠውን የአገልግሎት ጥራት ከፍ እንደሚያደርግለት ተማምኗል።


ደንበኞች የሚፈልጉትን የባንክ አገልግሎት ምቾታቸው እና ደህንነታቸው ተጠብቆ የሚስተናገዱበት የተለየ ክፍልና ቦታም በቅርንጫፉ ይገኛል።


የታላላቅ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሀብቶች ለባንክ አገልግሎት ወደ ቅርንጫፍ መምጣት ቢያስፈልጋቸው በልዩ ክብር የሚስተናገዱበት ቦታም መዘጋጀቱ ተነግሯል።


ይህን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓቢይ ቅርንጫፍ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ ሚኒስትሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ባለሀብቶች፣ የኩባንያ ባለቤቶች በተገኙበት ተመርቋል።


የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎቹ 1,937 እንደደረሱለት የተናገረ ሲሆን ከ41.3 ሚሊየን በላይ ደንበኞችም አሉኝ ብሏል።



ንጋቱ ሙሉ

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Comments


bottom of page