top of page

ነሐሴ 25፣2015 - የዘንድሮው ክረምት በአብዛኛው አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ የዘነበበት ነው ተባለ


የዘንድሮው የክረምት ወቅት በአብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ የዘነበበት ነው ተባለ።


የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በክረምቱ አጠቃላይ የአየር ግምገማና በመጪው በጋ በሚጠበቀው የአየር ጠባይ ትንበያ ዙሪያ ከሚመለከታቸው ጋር ዛሬ የግማሽ ቀን ውይይት አካሂዷል።


በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ከተካሄደው ከዚህ ውይይት በኋላም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ጋዜጣዊ መግለጫ ስጥተዋል።


በመግለጫቸው እንዳሉት ክረምቱ እንደተተነበየው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ቀደም ብሎ ነው የጀመረው።


መጠን እና ስርጭቱም በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች የተስፋፋ እና የተጠናከረ ነበር ብለዋል።


በሰሜን ምስራቅ እና ደቡብ ምዕራብ አንዳንድ አካባቢዎች ከዘነበው ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ ጎርፍ መከሰቱንም ተናግረዋል።


በአጠቃላይ የክረምቱ ዝናብ በምዕራብ አጋማሽ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ነበር ብለዋል።


በሰሜን ምስራቅ እና ምስራቅ አካባቢዎች ደግሞ መደበኛ እና ከመደበኛ በታች እንደሆነ ጠቅሰዋል ።


በቀጣዩ በጋ የሚኖረውን የአየር ጠባይ በተመለከተ ባለው ትንበያ ዙሪያም ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ አድርገዋል።


በዚህም በአብዛኛው የበጋ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ዝናቡ ቀድሞ እንደሚጀምር፣ በአወጣጥ ረገድ ደግሞ የዘገየ እንደሚሆን ተናግረዋል።


የበጋ ዝናብ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑት ደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል ብለዋል።


የምዕራብ አጋማሽ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ደግሞ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።በሰሜን ፣ በመካከለኛው፣ በምስራቅ እና ሰሜን ምዕራብ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል በአሁኑ ወቅት እየተስተዋሉ የሚገኙ የአየር ሁኔታ ክስተቶችን መነሻ አድርገው ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።ንጋቱ ሙሉ

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Comments


bottom of page