top of page

ነሐሴ 24፣2016 - ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያደርጓቸው ጥናቶችና ምርምሮች ቅድሚያ በሚሰጣቸው የኢትዮጵያ ችግሮች ላይ ያተኮሩ አይደለም



ትምህርት ሚኒስቴር እንደሚለው ተቋማቱ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ችግሮች ላይ የማያተኩሩት የበጀት እጥረትና ትኩረት የመስጠት ችግር ስላለባቸው ነው፡፡


በትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘረፍ የምርምርና ስርፀት ዴስክ ኃላፊ ዶክተር ሰራዊት ሃንዲሶ እንዳሉት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥናትና ምርምር ለማድረግ በጀት ይመድባሉ፡፡


ነገር ግን ጥናቶቹ ሀገሪቱን ወጥረው ይዘውኛል የምትላቸውን ችግሮች በመፍታት ላይ ያተኮሩ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት ትምህርት ሚኒስቴር ጥናትና ምርምሮች የተሻለ በጀት እንዲያገኙ ለማድረግና መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ እየተሰራ ነው ይላሉ፡፡


እነዚህ ስራዎች እንዲጠናቀቁ እቅድ ተይዞላቸዋል የተባለ ሲሆን በተለይም በ2017 በጀት ዓመት ፈጣን ስራ የሚያስፈልጋቸው ተብለው ለተለዩ ስራው ቅድሚያ ይሰራሉ ብለዋል፡፡


የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ በበኩላቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የበጀት ክፍተት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡


ነገር ግን ያላቸውን በጀት አብቃቅተው በአካባቢ የሚነገሩ ቋንቋዎች እንዲያድጉና ማህበረሰቡ በተሻለ መንገድ እንዲጠቀመው ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡


ትምህርት ሚንስቴር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተሻለ ትውልድ እንዲያፈሩ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ያሉት አቶ ኮራ ለዚህም ማሳያዎቹ ባለፉት ጊዜያት እየተተገበሩ ያሉ የካሪኩለም ቀረፃ እና የዩንቨርስቲዎች የራስ ገዝነት ስራ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡


ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመንግስት ከሚመደብላቸው በጀት ጎን ለጎን እራሳቸውም ሀብት ማመንጨት ላይ ወደፊት በስፋት ሊሰሩበት ይገባል ተብሏል፡፡


ሙሉ ዘገባውን በድምፅ ለማድመጥ ይህንን ማስፈንጠሪያን ይጫኑ... https://tinyurl.com/5e4tbrya


በረከት አካሉ

Comentarios


bottom of page