top of page

ነሐሴ 24፣2015 - ዳሸን ባንክ ከሁለት የአውሮፓ ተቋምት የ40 ሚሊየን ዶላር ብድር ማግኘቱን ተናገረባንኩ 40 ሚሊየን ዶላር ብድር ያገኘው ከእንግሊዙ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ('ቢ አይ አይ') እና ከኔዘርላንድሱ የስራ ፈጠራና ልማት ባንክ ከሆነው ኤፍ ኤም ኦ መሆኑ ለሸገር በላከው መግለጫ አስረድቷል፡፡


ሁለቱ ተቋመት እያንዳንዳቸው 20 ሚሊየን ዶላር በድምሩ 40 ሚሊየን ዶላር ብድር ለዳሸን ባንክ ማቅረባቸውን ተነግሯል፡፡


የብድር ገንዘቡ ኢትዮጵያ ለውጪ ገበያ የምታቀርበውን የግብርና ምርት ለማሳደግ እና በእጅጉ አስፈላጊ የሆነውን የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት ለማሻሻል ያስችላል ተብሎለታል፡፡


በተለይ በእርሻ ስራ ላይ ለተሰማሩ ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ ግብአቶችን በማሟላት ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ አስተዋጽኦ ያበረክታል መባሉን ሰምተናል፡፡


ዳሸን ባንክ ብድሩን በማግነቱ ዓይነተ-ብዙ አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ ለማቅረብ እንደሚያግዘው ጠቅሷል፡፡


ይህም በአመራረት፣ በማጓጓዝ እና በማቀናበር ሂደቶች ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ከውጭ ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ ማቅረብን ይጨምራል ተብሏል፡፡


በዚህ ትብብር 'ቢ አይ አይ' እና 'ኤፍ ኤ ምኦ' የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ በ2021 አዲስ ባወጣው የውጭ ማንዛሪ ማቀላጠፊያ መመሪያ መሠረት በኢትዮጵያ ለሚገኝ የፋይናንስ ተቋም በውጭ ምንዛሪ የቀረበ የረዥም ጊዜ ብድር ሲሰጡ የመጀመሪያዎቹ ናቸው ሲል ባንኩ አስታውሷል፡፡

በግብርና ለተሰማሩ የንግድ ተቋማት የሚቀርብ ፋይናንስ ከአበባ እስከ ቡና እና የቁም ከብት ድረስ የተሻሻሉ የአመራረት ዘዴዎችን ለማስተዋወቅ፣ ጥራትን ለማሳደግ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ለማሟላት እና እሴት ለመጨመር የጎላ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡


የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ የ40 ሚሊዮን ዶላሩ ብድር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእጅጉ እነደሚያስፈልግ አንስተው ለተገኘው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አለን" ሲሉ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡


ዳሸን ባንክ ያገኘው የ40 ሚሊዮን ዶላር ብድር በ3 ዓመት ውስጥ የሚመለስ መሆኑን ባንኩ ነግሯል፡፡


ንጋቱ ሙሉComments


bottom of page