12ኛ ክልል በመሆን የተመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 1ኛ የምስረታ ዓመቱን እያከበረ ነው፡፡
ቀድሞ የደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመባል ይጠራ የነበረው ክልል፤ በውስጡ ይነሱበት የነበሩት የተለያዩ ጥያቄዎችን ይመልሳል በሚል በተለያዩ ጊዜያት ህዝበ ውሳኔዎች ተደርገው ክልሉን በአራት መዋቅሮች እንደ አዲስ መደራጀቱ ይታወቃል፡፡
ከእነዚህ 4ቱ መካከል ‘’የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል’’ አንዱ ሲሆን በውስጡም 32 ብሄረሰቦች ይዟል፡፡
ክልሉ ከተመሰረተ አንድ ዓመት ደፍኗል፤ የክልሉ መንግስትም 1ኛ የምስረታ ዓመቱን እያከበረ ነው፡፡

ለመሆኑ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ይፈታል በሚል እንደ አዲስ የተዋቀረው ክልል በአንድ ዓመት ውስጥ ምን ሰርቷል?
ሲመሰረት የታለመለት ግቦች በማሳካቱ እየተሳካለት ነው ወይ፤ ምን መሳይ ፈተናዎችስ ገጠሙት ስንል የክልሉን መንግስት ጠይቀናል፡፡
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ሰሎሞን፤ ‘’ምንም እንኳ ያለፈው አንድ ዓመት እንደሽግግር ጊዜ የሚቆጠር ቢሆንም የክልሉን ህገመንግስት ከማርቀቅ እንሰቶ የተሰሩ ስራዎች ብዙ ናቸው’’ ብለዋል፡፡
እንዲሁም የገጠሙ ችግሮች እንደነበሩ ያነሳሉ፡፡
በቀድሞ ክልል ከአደረጃጀት ጋር በተያያ ይነሱ የነበሩ ልዩነቶች መፍታት ክልሉ ሲመሰረት ከያዛቸው እቅዶች መካከል የነበረ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

‘’በእቅዱ መሰረትም በዚህ አንድ ዓመት በተለያዩ ብሔረሰቦችን መካከል አንድነት እንዲጠነክር ሰርተናል’’ ብለውናል፡፡
በክልሉ ‘’ሰላም ማስፈን’’ ሌላው የተያዘው ዓለማ እንደነበረ ወ/ሮ ሰናይት ተናግረዋል፡፡
‘’በተለይም የፖሊስ መዋቅሩ ላይ በመስራት በአሁን ላይ በክልሉ አንፃራዊ የሚባል ሰላም ለማምጣት ተችሏል’’ ብለዋል፡፡
‘’ከኢኮኖሚ አንጻርም በተለይ በክልሉ በስፋት የሚመረተውን የቡና ምርት፣ ቱሪዝም እና የእንስሳት ሀብትን ጨምሮ በዞኖቹ የነበረውን የመልማት አቅም ላይ በብርቱ ተሰርቶ ለውጦች መጥተዋል’’ ብለዋል፡፡
በክልሉ በዚህ አንድ ዓመት ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ችግሮች በክልሉ እንደገጠሙ ጠቁመዋል፡፡
‘’ጥቂት ቡደኖች ወይም ግለሰቦች የራሳቸው የሆነን ፍላጎት የህዝብ ጥያቄ አድርገው መንቀሳቀሳቸው ከገጠሙን ችግሮች መካከል አንደኛው ነው’’ ሲሉ ነግረውናል፡፡
በክልሉ በሚኙ ዞኖች ውስጥ የሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞች ለወራት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው በተለያየ ጊዜ ይሰማል፡፡

በተለይ የወላይታ ዞን በዚህ እየተቸገረ እንደሆነ መነግሩ የሚታወስ ሲሆን የክልሉ የመንግስተ ኮሚዩኒኬሽን ሀላፊ ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞነንን ስለጉዳይ ጠይቀናል፡፡
ሀላፊዋ ሲመለሱም፤ ክልሉ በፌደሬሽን ምክር ቤት በተመደበለት የበጀት ቀመር መሰረት ለዞኖቹ እንደሚያከፋፍል ገልፀው፤ ችግሩ እየተፈጠረ ያለው በዋናነት ዞኖቹ የውስጥ ገቢያቸውን በተገቢው አሟጠው አለመጠቀማቸው እንደሆነ አንስተዋል፡፡
‘’ክልሉ ጉዳዩ በቅርበት እየተከታተለው ነው ለዚህም ይረዳ ዘንድ በጋራ ገቢዎችንም ዞኖቹ እንዲጠቀሙ ተደርጓል’’ ብለዋል
የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል የመሰረቱት የጌዲኦ፣ የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የኮንሶ፣ የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ልዩ ወረዳዎች ናቸው።
ሙሉ ዘገባውን በድምፅ ለማድመጥ ይህንን ይጫኑ
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comentários