የስምምነት የፊርማ ስነስርዓቱም በዛሬው እለት በዓባይ ባንክ ዋና መስሪያቤት ተከናውኗል።
በስምምነቱ መሠረት የሳፋሪኮም ኤምፔሳ ደንበኞች የዓባይ ባንክ ቅርንጫፎችን በመጠቀም ገንዘብ ለማውጣትና ለማስገባት ይችላሉ ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ደንበኞች ከዓባይ ባንክ ሂሳባቸው ወደ ኤምፔሳ ሂሳባቸው፣ ከኤምፔሳ ሂሳባቸው ወደ ዓባይ ባንክ ሂሳባቸው ገንዘብ ማስተላለፍ እንዲችሉ፣ የአገልግሎት ክፍያዎችን እንዲከፍሉ፣ የሂሳብ መረጃዎችን እንዲያዩ፣ የአየር ሰዓት እንዲገዙ እና ሌሎችንም የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶች እንዲያገኙ የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡
ዓባይ ባንክ ከ500 በላይ ቅርንጫፎች እንዳሉት የተናገረ ሲሆን ቅርንጫፎቹ በሌሉባቸው አካባቢዎች በኤምፔሳ ኤጀንቶች በኩል የፋይናንስ አገልግሎት ማቅረብ እንደሚያስችል ተነግሯል።
ስትራቴጂያዊ ስምምነቱን ዓባይ ባንክ የሳፋሪኮም ኤምፔሳ ከፍተኛ ወኪል (ሱፐር ኤጀንት) በመሆን የሞባይል ባንኪንግ እና የወኪል ባንኪንግ ስራዎችን በቀለጠፈ መንገድ መስጠት ያስችላል ተብሏል።
የሳፋሪኮም ስልክ ቁጥር ያላቸው የዓባይ ባንክ ደንበኞች ወደ ባንኩ ቅርንጫፎች ጎራ በማለት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማስደረግ ይችላሉ ተብሏል።
የስምምነት ፊርማውን የዓባይ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ የኋላ ገሠሠና የሳፋሪኮም ኤምፔሳ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፖል ካቫቩ ተፈራርመውታል።
ሀላፊዎቹ በሰጡት አስተያየት የተጀመረው የስራ አጋርነት ስምምነት በማጠናከር ደንበኞችን የዘመናዊ የባንክ አገልግሎት እና የክፍያ ስርአት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል እንደሚሰሩ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
ዓባይ ባንክ ለደንበኞቹ የባንክ አገልግሎቶችን በቀለሉ እና በዘመኑ መንገዶች ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን የተናገረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም 2.5 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳሉት ተናግሯል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የሞባይል የገንዘብ አገልግሎት እንዲሰጥ ከብሔራዊ ባንክ ፍቃድ እንደተሰጠው የተናገረው ኤም-ፔሳ ከኬንያ በተጨማሪ በሌሎች አገሮች የሚሰራ ሲሆን ኢትዮጵያ ስምንተኛ መዳረሻው ነች፡፡
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
コメント