top of page

ነሐሴ 22፣2016 - የእምባ ጠባቂ ተቋም የባህርዳር ቅርንጫፍ፣ ማን ይነካኛል በሚሉ አመራሮች ምክንያት ስራ መስራት አልቻልኩም አለ

የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ የማይፈጽሙ፣ ለህግ የበላይነት የማይገዙ፣ ማን ይነካኛል በሚሉ አመራሮች ምክንያት ስራ መስራት አልቻልኩም አለ፡፡


በአማራ ክልል የሚገኙ በርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን የሚመሩ አመራሮች «ለምን እነካለው» በሚል የፍርድ ቤቶችን ትዕዛዝ የማይቀበሉ፣ የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የሚሰጣቸውን ምክረ ሃሰብ የማይፈጽሙ፤ የስራ ኃላፊዎች እንቅፋት እንደሆኑበት ጽህፈት ቤቱ አስረድቷል፡፡


የእነዚህን አመራሮች መስሪያ ቤት በቅርቡ ይፋ እንደሚደርግ የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጋሻነው ደሴ ነግረውናል፡፡


«የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣውን ህግ አልፈጽም ለህግ የበላይነትም አልገዛም ምን ይነካኛል» ለሚሉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ልዩ ሪፖርት ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት እና ለክልሉ ምክር ቤት እያሰናዱ እንዳሉም የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ጋሻነው ደሴ ነግረውናል፡፡


የመንግስት ሥርዓት ተጠቃሚ የሚሆነው እራሱ ህግን ሲያከብር ነው ያሉት ኃላፊው እሱ ህግን ካላከበረ ሌላውን ማስከበር አይችልም ሲሉ ነግረውናል፡፡


«እኛ የዴሞክራሲ ተቋማት ያለን ጉልበት ህግ ነው ይሁንና ችግሮችን መርምረን መስረጃዎችን አሰናድተን እንዲፈፀሙ ህግ ለሚያስገድዳቸው የስራ ኃላፊዎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጣለው ግዴታ አለ አንዳንዶቹ በከፋ መንገድ የማያስፈጽሙ የፍርድ ቤትንም ትዕዛዝ የማይፈጽሙ አሉ ይህም የህዝብ ተወካይዎችን ምክር ቤት ስልጣን መናቅ ነው» ብለዋል ኃላፊው፡፡


‘’አትንኩኝ ባይነቱ በጣም ሰፊ ነው’’ ያሉት አቶ ጋሻነው ‘’አንዳንድ የስራ ኃላፊዎች እኛ ከህዝብ የተቀበልነውን እንዲያስፈጽሙ ስንጣይቃቸው ፍቃደኛ አይሆኑም ይሁንና በክልል ከፍተኛ የአመራር ለውጥ አለ ያኔ እነሱ ከስልጣን ሲወርዱ ያለ ምክንያት ከደረጃ ዝቅ ተደርጊያለሁ ገላግሉኝ’’ ብለው ፍትህ ፍለጋ ይመጣሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡



ያሬድ እንዳሻው

Comentários


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page