top of page

ነሐሴ 22፣2016 - በ2016 የትምህርት ዘመን በአማራ ክልል 3.4 ሚሊዮን ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመጨረስ አልቻሉም አልያም ጭራሽ ትምህርት ቤት አልገቡም

በ2016 የትምህርት ዘመን በአማራ ክልል 3.4 ሚሊዮን ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመጨረስ አልቻሉም አልያም ጭራሽ ትምህርት ቤት አልገቡም፡፡


የክልሉ ትምህርት ቢሮ እንዳለው ከእነዚህ ውስጥ 2.5 ሚሊዮን ተማሪዎች በዚህ ወቅት ትምህርት ቤት ያልሄዱ ሲሆን 900,000 ደግሞ ትምህርታቸው ጀምረው ሳይጨርሱ አቋርጠዋል፡፡


እነዚህ ተማሪዎች በ2017 የትምህርት ዘመን ወደ ትምህርት እንዲመጡና ያለፋቸው የትምህርት ጊዜ ለማካከስ አቅጄ እየሰራሁ ነው የሚለው የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለዚህም ከወላጆች ጋር እየመከርሁበት ነው ብሏል፡፡


#የአማራ_ክልል_ትምህርት_ቢሮ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደግሰው መለሰ ‘’ከወላጆች ጋር በመነጋገር ተማሪዎች ማካካሻው ትምህርት ወስደው ወደ ቀጣይ ከፍል እንዲገቡ አልያም በ2017 የትምህርት ዘመን ዳግም ያልተማሩትን ክፍል መድገም በሚለው ዙሪያ ነው’’ ሲሉ ነግረውናል፡፡


የክልሉ ትምህርት ቢሮ የ2017 የትምህርት ዘመን ምዝገባ የጀመረ ሲሆን 7 ሚሊዮን ተማሪዎች በዚህ ወቅት ለማስተማር አቅዶ ለመመዝገብ ስራ ጀምሯል፡፡


በክልሉ ያለው #ግጭት ለምዝገባው እንቅፋት እንዳይሆን ምን ተሰርቷል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡስ ምን ተደርጓል ብለን አቶ ደግሰውን ጠይቀናቸዋል፡፡

‘’ልጆች በምን ሁኔታ ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ቢሮው እየሰራ ነው’’ ያሉት ኃላፊው ለዚህ ስራ መምህራን ጭምር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡


‘’የልጆቹ እድሜ በዚህ ሰዓት መዋል ያለበት በትምህርት ገበታ ነው ማንኛውም አካል ይህንን ተገንዝቦ ከቢሮው ጋር በትብብር ሊሰራ ይገባል’’ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡


ከዚህ ባለፈም ክልላዊና ሀገራዊ ፈተና ያመለጣቸው #ተማሪዎች አዘጋጅቶ በልዩ ሁኔታ እንዲፈተኑ እየሰሩ መሆኑን ነግረውናል፡፡


ነሃሴ 20 በተጀመረው የአማራ ክልል የ2017 የተማሪዎች ምዝገባ በመጀመሪያው ቀን ብቻ 217,000 ተማሪዎች በ374 ትምህርት ቤቶች መመዝገባቸውን ሰምተናል፡፡


‘’የክልሉ ትምህርት ቢሮ ማንኛውም አካል ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱና ትምህርታቸውን ብቻ እንዲማሩ ሊያደርግና ይህንን ስራ ሊደግፍ ይገባል’’ ሲሉ አቶ ደግሰው አሳስበዋል፡፡


በረከት አካሉ

Comments


bottom of page