የኦሞ ወንዝ ሙላት ባስከተለው መጥለቅለቅ በውሃ ተውጠው የሚገኙ ከ12,000 በላይ ሰዎችን ከአካባቢው ማውጣት እንዳልቻለ የዳሰነች ወረዳ ተናገረ፡፡
በተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ የሚያስከትለው የኦሞ ወንዝ በክረምቱ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ከወንዙ 1.5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የውሃ መጥለቅለቅ አስከትሏል፡፡
የወረዳው ዋና ከተማ የሆነችው የዳሰነች ከተማን አጥለቅልቋል በከተማዋና በዙሪያዋ ካሉ 34 ቀበሌዎች ከ79,000 በላይ ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ ማድረግ መቻሉን የነገሩን የዳሰነች ወረዳ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ መሳይ ሊበን ናቸው፡፡
አቶ መሳይ እንደሚሉት አብዛኞቹን ተጎጂዎች ማውጣት ቢቻልም አሁንም ድረስ በ2 ወረዳ ውስጥ ያሉ ከ12 ሺህ በላይ አሁንም ድረስ በውሃ ተውጠው ይገኛሉ፤ በእኛ አቅም ማውጣት አልቻልንም ብለዋል፡፡
ሰዎቹን ለማውጣት ሄሊኮፍተር ወይም ጀልባ ያስፈልጋል፣በአፋጣኝ እንዲቀርብልን የፌድራሉን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ብንጠይቅም ምላሽ ማግኘት አይቻልንም ብለውናል፡፡
የኦሞ ወንዝ ሙላት በየጊዜው አደጋ ያስከትላል የሚሉት የመንግስት ዋና ተጠሪው አሁን አደጋውን ያባባሰው ከጎረቤት ኬንያ ድምበር ያለው የቱርካና ሃይቅ ከኦሞ ወንዝ ጋር በመቀላቀሉ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ጊዜያዊ የመገደብ ስራ ቢሰራም በዘላቂነት ችግሩን ማስቆም የሚቻለው የፌድራሉ መንግስት ባለሙያ መድቦ ተገቢው ስራ ሲሰራ ነው፣ በዚህም በኩል ጥያቄ ብናቀርብም እስካሁን መጥቶ ያየን እንኳን የለም ብለዋል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ሸገር፤ የፌድራሉን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለመጠየቅ ቢሞክርም ለጊዜው ምላሽ አላገኘም፡፡
የወንዙ ሙላት በዚሁ ከቀጠለ የዳሰነች ከተማን ሙሉ ለሙሉ ሊያወድማት ይችላል ይህ ከመሆኑ በፊት ድረሱልን ብለዋል፡፡
ምንታምር ፀጋው
Comments