የኦሮሞ ፌደራሊሰት ኮንግረንስ ፓርቲ(ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) በኦሮሚያ ክልል ያሉን ወደ 400 የሚጠጉ ቢሮዎቻችን ተዘግተዋል አሉ፡፡
ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ከ50 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት የያዘው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በበኩሉ፤ ይህም በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ ትግል አንዲጠብ እና የትጥቅ ግጭት እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል ብሏል፡፡
የኦሮሞ ኮንግረንስ ፓርቲ አፌኮ የህዝብ ግኝኑነት ሃላፊ ሱልጣን ቃሲም ‘’ከ5 ዓመት በፊት የለውጡ ሰሞን መንግስትን ተማምነን ለሰላማዊ ትግል ምቹ ሁኔታ ይኖራል በሚል ተነሳሽነት 206 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን ከፍተን ነበር አሁን 203 ተዘግተውብን የቀሩን ሶስት ጽህፈት ቤቶች ናቸው’’ ብለዋል፡፡
አቶ ሱልጣን ቃሲም ‘’የቢሮዎቻችን መዘጋት እና የአባላቶቻችን መታሰር በኦሮሚያ ክልል ለሰላማዊ ትግል ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ያሳያል’’ ብለዋል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ለሚ ገመቹ ‘’በለውጡ ሰሞን በተስፋ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጋ ቢሮዎች ከፍተን የነበረ ቢሆንም አሁን አንድም ቢሮ የለንም’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሃላፊው የፓርቲው ‘’ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችም በኢ-መደበኛ እና በመደበኛ እስር ቤቶች በእስር ላይ ናቸው’’ ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በበኩሉ ፓርቲዎቹ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና እኔ ብቻ ሳልሆን መንግስትም ያውቃል ብሏል፡፡
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ ‘’በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ትግል እያደረጉ ያሉ ፓርቲዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጫና በክልሉ የትጥቅ ግጭት እንዲበረታ ምክንያት ሆኗል’’ ብለዋል፡፡
‘’በፓርቲዎቹ ላይ እየደረሰ ያለው ጫና የትጥቅ ትግሉ እንዲባባስ እና ሰላማዊ ትግሉ እንዲጠብ እያደረገ ነው’’ ያሉት ሰብሳቢው ‘’ይህ እንዲፈታም መንግስትን በተደጋጋሚ እየጠየቅን ነው’’ ብለዋል፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎቹ እየደረሰብን ነው ባሉት ጫናም ከመንግስት ጋር የሚደረግ ውይይትን ጨምሮ ከሀገራዊ ምክክር እራሳቸውን አግልለዋል ሲሉ ሰብሳቢው ነግረውናል፡፡
ሸገር ኤፍኤም በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን እና የክልሉ መንግስት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡
ይሁንና ከወራቶች በፊት የ11 ወር የስራ ክንውናቸውን ሪፖርት ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ያቀረቡት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ በፖለቲካ ፓርቲ አባላት ላይ እስራት እየተፈጸመባቸው እንዳለ ተናግረው ቦርዱ እንዲለቀቁ ለክልል ፖሊስና ለፀጥታ ተቋማት የሚፅፋቸው ደብዳቤዎችም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አስደርተዋል፡፡
ይህም የፖለቲካ ምህዳሩ ላይ ጫና ማሳደሩን ተናግረው ነበር፡፡
ያሬድ እንዳሻው
Kommentare