ማክሰኞ ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም 25 ኢትዮጵያውያን እና 2 የመናዊያንን አሳፍራ ከጅቡቲ የተነሳችው የስደተኞች ጀልባ ዱባብ አቅራቢያ ልዩ ስሙ ባኒ አል ሃካም አከባቢ ተገልብጣ መስጠሟን በየመን የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት(አይኦኤም) ዘግቧል።
አደጋውን ተከትሎም 13 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ የተቀሩት 14ቱ ደግሞ ደብዛቸው ጠፍቷል ተብሏል።
ከሟቾች መካከል አስራአንዱ ወንዶች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው።
የሟቾቹ አስከሬን በዱባብ አከባቢ አልሹራ አቅራቢያ የሚገኘው ባብ-ኤል መንደብ የባህር ዳርቻ ላይ ተገኝቷል።

በስፍራው ያሉ የነፍስ አድን ሰራተኞች የቀሪዎቹን ስደተኞች አካል የማፈላለግ ስራ እስከአሁን እንደቀጠሉ ነው።
በዚህ መስመር በሚያጋጥመው ከባድ ማዕበል ምት እና የጀልባ አቅም ውስንነት ምክንያት በተደጋጋሚ የጀልባ መሰበር፣ መገልበጥ እና መስጠም አደጋ እየደረሰ ይገኛል።
ባለፉት 10 ዓመታት በዚህ ምስራቃዊ መስመር ላይ ብቻ 693 ሰዎች በባህር ላይ የሰጠሙትን ጨምሮ 2,082 የስደተኞች ሞት ተዝግቧል።
በአሁን ወቀት በየመን ያለው አለመረጋጋት እየጨመረ ቢሄድም ከዚህ በተቃራኒ ዜጎች በህገ-ወጥ መንገድ ወደዚህ ስፍራ የሚያደርጉት ጉዞ እየተበራከተ መምጣቱን አይኦኤም(IOM) ዘግቧል።
ንጋቱ ሙሉ
Comments