ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በቤተሰብ የሚጀመሩ የንግድ ስራዎች እድሜ የማይኖራቸው ለምንድነው?
በተለያዩ ጊዜያት በርከት ያሉ የንግድ ተቋማት ተከፍተው የት ይደርሳሉ ሲባሉ፣ መስራቾቹ ሲያልፉ የንግድ ተቋማቱም ሲከስሙ ይታያል፡፡
ለዚህ በርከት ያሉ ምክንያቶች ሲጠቀሱ አንዱና ዋንኛው ምክንያት ግን የተከፈተው የንግድ ተቋማት ጥሩ ተረካቢ ቤተሰብ ባለማግኘት እንደሆነ ይነገራል፡፡
አቶ አየለ አሰፋ አብዛኛው የስራ ዘመናቸውን በንግድ አስተዳደር ያሳለፉ ሲሆን በቤተሰብ ንግድ ዙሪያ የሚያተኩር መፅሐፍ ወደ አማርኛ መልሰው አሳትመዋል፡፡
አብዛኛው አውሮፓ እና አሜሪካ ውስጥ ያሉ ግዙፍ የንግድ ድርጅቶች የሚተዳደሩት በቤተሰብ ንግድ ነው ያሉት አቶ አየለ በእነዚህ ሀገራት ካሉ የንግድ ድርጅቶች መካከል 60 ከመቶ የሚሆኑት የቤተሰብ ንግድ ናቸው ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች አብዛኛው ጊዜ ስራቸው ሲሰሩ ለብቻቸው ነው ቤተሰቦቻቸው የሚፈልጉት እንዲረከቧቸው ሲፈልጉ ነው ብለዋል፡፡
ይህ ነገር አሁንም አለ የሚሉት አቶ አየለ መፅሐፉን ለማዘጋጀት ሲንቀሳቀሱ ያናገሯቸው ነጋዴዎች አብዛኛዎቹ ንግዳቸው ውስጥ ቤተሰባቸውን አያሳትፉም ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
የዋሪት ሙሉ ጥላ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ መስራች ለገሰ ዋሪት ዘሪሁን በበኩላቸው ወላጆች የንግድ ስራዎች ሲሰሩ በብዛት ልጆች እንዲሳተፉ አያደርጉም፡፡
ይህ ስህተት ነው የሚሉት አቶ ለገሰ እሳቸው የመሰረቱት ኩባንያ ከ30 ዓመት በላይ የሆነው ልጆቻቸው አብረዋቸው እንዲሰሩ በማድረጋቸው መሆኑን ነግረውናል፡፡
የዋሪት ማኔሺንግ ዳይሬክተር ትህትና ሙሉ ሸዋ ለገሰ ቤተሰቦች ልጆችን ሲያሳድጉ ከትምህርት ጎን ለጎን የሚሰሩት ስራ በሚገባ እንዲያውቁት ሊያደርግ ይገባል ስትል ትመክራለች፡፡
ከዚህ ባለፈም ቤተሰቡና ስራው የሚመራበት ህግ ከሌለ የወደፊት እጣ ፈንታው አጠያያቂ ነው የምትለው ወይዘሮ ትህትና ከዚህ በተቃራኒው መንገድ ከሆነ አመታትን የሚተላለፍና ጠንካራ ድርጅትን ማዋቀር እንደ ቤተሰብ ይቻላል ተብሏል፡፡
አቶ አየለም ይህንን ሀሳብ የሚደግፉ ሲሆን የቤተሰብ ንግድ ሲቋቋምና ሲመሰረት ቤተሰቡ ስራው የሚመራበትና ወደፊት እንዴት ሊሄድ እንደሚገባ የሚያሳይ ህግ ሊያፀድቅ ይገባል ያሉ ሲሆን ይህ ከሆነ የስራው ቀጣይነት አስተማማኝ ይሆናል ሲሉ ይመክራሉ፡፡
በረከት አካሉ
Comments