በሱዳን የጣለ ዶፍ ዝናብ በጥቂቱ ለ17 ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑ ተሰማ፡፡
ዶፍ ዝናቡ እጅግ በርካታ ቤቶችን መደረማመሱን አልባዋባ ፅፏል፡፡
ከባድ መጥለቅለቅም ማስከተሉ ተሰምቷል፡፡
አደጋው የደረሰው በናይል ግዛት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ 170 ሰዎች ደግሞ አካላዊ ጉዳት ገጥሟቸዋል ተብሏል፡፡
ባለፈው 1 ወር በሱዳን በደረሰ ጎርፍ የሟቾቹ ብዛት 30 መድረሱ ታውቋል፡፡
ዶፍ ዝናብ እና ጎርፉ ለሱዳን በጦርነቱ ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባታል ተብሏል፡፡
የእስራኤል ፖሊስ በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የምርመራ ብርበራ ማድረጉ ተሰማ፡፡
የእስራኤል ፖሊስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ብርበራ የተከናወነው የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ልጅ ዲፕሎማት ሳይሆን የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ወስዷል መባሉን ለማጣራት ነው ተብሏል፡፡
ፖሊስ በዚሁ ጉዳይ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ብርበራ ስለማድረጉ መግለጫ እንዳወጣ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
እንደሚባለው ቀደም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ኤሌ ኮኸን ለኔታንያሁ ልጅ እና ዲፕሎማት ላልሆኑ የሊኩድ የፖለቲካ ማህበር የተወሰኑ አባላት የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እንዲሰጥ አዘው ነበር፡፡
ኤሊ ኮኸን በአሁኑ መንግስት የመሰረተ ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር እንደሆኑ መረጃው አስታውሷል፡፡
ጃፓን በ2 ከባባድ ርዕደ መሬቶች መመታቷ ተሰማ፡፡
ኪየሹ የተባለችዋ ደቡባዊ ደሴት በርዕደ መሬት መለኪያ ሬክተር ስኬል 6. 9 እና 7.1 ሆነው በተመዘገቡ ነውጦች መመታቷን ገልፍ ኒውስ ፅፏል፡፡
በነውጦቹ ስለደረሰው ጉዳት ለጊዜው በዝርዝር የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
WA እንደፃፈው ደግሞ በከባዶቹ ርዕደ መሬቶች ምክንያት የባህር ማዕበል /ሱናሚ/ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰምቷል፡፡
ጃፓን ርዕደ መሬት የሚደጋገምባት አገር ነች፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments