ነሐሴ 2፣2016 - መንግስት ለሰራተኞቹ አደርጋለው ያለው የደመወዝ ጭማሪ እንዳይዘገይ ኢሰማኮ ጠየቀ
- sheger1021fm
- Aug 8, 2024
- 1 min read
መንግስት የደመወዝ ጭማሪ አደርጋለው ቢልም ገበያው በዚሁ ከቀጠለ ከሰራተኛው ከአቅሙ በላይ ሊሆንበት ይችላል ሲል የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን ተናገረ፡፡
ኮንፌደሬሽኑ #የማክሮ_ኢኮኖሚ ማሻሽያው በታወጀ በማግስቱ ስለሆነ ለመንግስት ሰራተኞች ይደረጋል የተባለው የደመወዝ ማሻሽያ እንዳይዘገይም ጠይቋል፡፡
የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሽያ ተከትሎ በገበያ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየታየ መሆኑን የተናገረው ኮንፌደሬሽኑ ይህ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ለመንግስት ሰራተኛው ይደረጋል የተባለው የደመወዝ ማሻሽያ ዋጋ የለውም ሲሉ የኮንፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዘዳት አያሌው አህመድ ተናግረዋል፡፡
የገበያው ዋጋ ቁጥጥር በሌለበት በተለመደው አይነት መልኩ ከተገቢው በላይ ጭማሪ የሚሳይ ከሆነ ይጨመራል በተባለው ደሞዝ መቋቋም የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብለዋል ምክትል ፕሬዝዳንቱ፡፡
የነጋዴው ማህበረሰብም መንግስት የሚያወጣውን መመርያ ተክትሎ የማይጎዱበትን ጭማሪ ካልሆነ በስተቀር በዘፈቀድ ምርቶች እየተደበቁ ሰራተኛው ለአላስፈላጊ ወጪ የሚደረግ ከሆነ አሁንም መልሶ ከችግር የሚወጣበት ሁኔታ አይኖርም ሲሉ አያሌው አህመድ ተናግረዋል፡፡
መንግስትም በቂ #የደመወዝ_ማሻሽያ ፤ ነጋዴውም ምክንያታዊ ጭማሪ ካላደረገ በገበያው ይበልጥ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል ተብሏል፡፡
ለዚህ ደግሞ ቁጥጥር ማድረግ ያለበት መንግስት እና ህብረተሰቡ ነው ሲሉ አቶ አያሌው አህመድ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን ገበያው ላይ ምን እንዳለ መንግስት ያውቃል ምክንያቱም የዋጋ ንረቱ ሰራተኛውን አልፎት ሄዷል ለዚህም የደመወዝ ማሻሽያው መዘግየት የለበትም ሲል አሳስቧል፡፡
ባለፈው ስለ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሽው ማብራርያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ታች ላለው የመንግስት ሰራተኛ አስከ 300 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ እንደሚደረግ ተናግረው ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ ወደ 2.5 ሚሊዮን የሚጠጋ የመንግስት ሰራተኛ እንዳለ ይነገራል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሽያው ከተደረገ ወዲህ ዘይትን ጨምሮ የፍጆታ እቃዎች በሀገር ውስጥ በሚመረቱ እና ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጭማሪ ተስተውሏል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments