ነሐሴ 17፣2016 - ባለፉት 2 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የህትመት ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ይነገራል
- sheger1021fm
- Aug 23, 2024
- 1 min read
የዘርፉ ባለሞያዎችም በዚህ ምክንያት አንባቢ እንዳይጠፋ ስጋት አለ ከወዲሁ መላ ሊበጅለት ይገባል የሚል ተደጋጋሚ ስሞታ ሲያነሱ ይደመጣል፡፡
እንዲህ ያለው ጥያቄ መልስ ሳያገኝ ይባሱኑ መንግስት ከሰሞኑ በመፅሐፍት ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ከተናገረ ወዲህ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን ጉዳዩ አስደንግጧቸው ለመመካከርም ተቀምጠው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ አታሚና አሳታሚ ማህበር ይህ የመንግስት ስራ የኢትዮጵያን የህትመት ኢንዱስትሪንና ንባብን የገደለ ነው ሲል ኮንኖታል፡፡
የህትመት እንዲስትሪው ታሟል በዚህ ላይ ሌላ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጨመር ዘርፉን ወደሞት መሸኘት ነው ያሉን የማህበሩ ዋና ፀሐፊ አቶ ሀይማኖት አስመራው ከዚህ በፊት በ2,000 ብር እስከ 10 መፅሐፍት ድረስ መገበያየት ይቻል ነበር አሁን በዚህ ዋጋ ቢበዛ 3 መፅሐፍት ብቻ ነው የሚገዛው ይላሉ፡፡
ገቢያ ውስጥ መፅሐፍት በመወደዳቸው አንባቢ እየጠፋ ነው ያሉት አቶ ሀይማኖት የሚነበቡ መፅሐፍትም ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል፡፡
በዚህ ምክንያት አሁን የሙሉ ጊዜ ደራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ቁጥራቸው እጅግ ተመናምኗል ያለ ሲሆን ወቅታዊው ህትመት ስራ ለአሳታሚያኑም ከዘርፉ እንዲወጡ እያደረገ ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡
መንግስት ቢቻለው በመጽሐፍት ህትመት ኢንዱስትሪው የጣለውን ተደራራቢ ታክስ ያንሳ ይህ ካልሆነ ደግሞ መጠኑን ይቀንስ የሚሉት አቶ ሀይማኖት ከዚህ ዘርፍ የሚያገኘው ገቢ ብዙም እርባና ያለው አይደለም፡፡
ችግሮቹ እንዲፈቱ ካስፈለገና መንግስት ነገ ላይ የተሻለ ትውልድ ኢትዮጵያ እንድታገኝ የሚሻ ከሆነ በህትመት ዘርፍ ለተሰማሩት ባለሃብቶች ድጎማ ባይደረግም እንኳን መንግስት በሚልዮን ዶላር ወጪ በማድረግ በውጪ ሀገራት የሚያሳትማቸው የመማሪያ መጽሐፍት እና ሌሎች የህትመት ውጤቶች ለሀገር ውስጥ ተቋማት ሊሰጥ ይገባል ያሉት የኢትዮጵያ አታሚና አሳታሚ ማህበር ጸሐፊው ይህ ቢያደርግ ቢያንስ ዘርፉ እንዲነቃቃ ማድረግ ይችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ሙሉ ዘገባውን በድምፅ ለማድመጥ ይህንን ማስፈንጠሪያን ይጫኑ... https://tinyurl.com/yc84ntzk
በረከት አካሉ
Comentarios