top of page

ነሐሴ 17፣2016 - በጅቡቲ ያለው ሙቀት ከፍተኛ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ለጭነት የሚሄዱ አሽከርካሪዎች ለሞት ጭምር እየተዳረጉ መሆኑ ተነግሯል

በጅቡቲ ያለው ሙቀት ከፍተኛ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ለጭነት የሚሄዱ አሽከርካሪዎች ለሞት ጭምር እየተዳረጉ መሆኑ ተነግሯል፡፡


ባለፉት ሁለት ወራት ብቻም 5 የከባድ ጭነት መከና አሽከርካሪዎች፤ በመኪናቸው ውስጥ እና ከመኪናቸው ስር ሞተው ተገኝተዋል ተብሏል፡፡


የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር፤ ለአሽከርካሪዎቹ በሙቀት መሞት ባለሀብቶችን ተጠያቂ አድርጓል፡፡


የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ሰለሞን ዘውዱ ጉዳዩን ሲያብራሩም፤ ‘’አሽከርካሪዎቹ ለሞት የሚዳረጉት የጭነት ወረፋቸው ሳይደርስ ባለሀብቶቹ ወደ ጀቡቲ እንዲሄዱ ስለሚያደርጓቸው ነው’’ ብለዋል፡፡


አሽከርካሪዎቹ ወረፋቸው ሳይደርስ ወደ ጅቡቲ ተልከው እስከ 15 ቀን የሚቆሙ እንዳሉም ተናግረዋል፡፡


በዚህም ‘’በተፈጥሮ ሙቀት መቋቋም የመይችሉ እና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው አሽከርካሪዎች ለሞት ጭምር እየተዳረጉ ነው’’ ብለውናል፡፡


‘’አሽከርካሪዎቹ የመጫን ወረፋቸው መድረሱን በስልካቸው መልዕክት ይደርሳቸዋል’’ ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ ስለዚህ መሄድ የሚገባቸው አንድ ወይም ሁለት ቀን ሲቀራቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡


የመኪና ባለቤቶች አሽከርካሪዎቹን የመጫን ወረፋቸው ሳይደርስ የሚልኩበት ምክንያት ‘’ምናልባትም መሀል ከተማ ላይ የማቆሚያ(የፓርኪኒንግ) ላለመክፈል እና በሌሎች በማናውቃቸው ምክንያቶች ነው’’ ሲሉ ያስረዳሉ፡፡


በመኪና በባለንብረቶች የተቋቋመው የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ማህበር በበኩሉ፤ ተሽከርካራች በጅቡቲ ወደብ እስከ 6 ቀን ሊቆዩ ይችላሉ ይህ የሚሆነውም በአብዛኛውም ጊዜ ኮንቴይነር ሳይቀርብ ሲቀር እንደሆነ ተናግሯል፡፡


የማህበሩ የህዝብ ግኑኝነት ሀላፊ ደጀኔ ሎጬ፤ ‘’በጀቡቲ ወደብ ያለው ሙቀት ለአሽከርካሪዎች ከባድ እንደሆነ እንረዳለን፣ ተሽከርካሪዎች እዛ ብዙ ቀናት በቆዩ ቁጥር ባለሀብቱም ወጪ ሊያስወጡ የሚችሉ አጋጣሚዎችም ሊኖሩ ይችላሉ፤ በዚህም ባለሀብቱም መኪኖቹ እዚያ ሄደው እንዲቆሙ አይፈልጉምም’’ ብለውናል፡፡


‘መሀል ከተማ ላይ ፓርኪንግ እንዳይከፍሉ ተብሎ ነው’ በሚል ከከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር በኩል ለተጠቀሰው ምክንያትም፤ እንደማህበራቸው እንደማያውቁት እና ምናልባትም በተለየ መልኩ ሊታይ የሚችል ጉዳይ ሊሆን ይችላል ሲሉም ተናግረዋል፡፡


በዚህ ወቅት በጅቡቲ ያለው ሙቀት ከ40 እስከ 50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርስ እንደሆነም ተነግሯል፡፡


የጅቡቲ መንገድ ከሙቀቱም ባለፈ ብዙ ችግር ያለበት በመሆኑ አሽከርካሪዎች በብዙ እየተቸገሩ እንደሆነ የሚያነሱት በመስመሩ ለረጅም አመታት የመመላለስ ልምድ ያላቸው እና የዩኒቲ ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አክሲዮን ማህበር ስራ አስኪያጅ ደረጄ ጌታቸው ናቸው፡፡


የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ‘’አሽከርካራች የመጫን ተራቸው ሳይደርስ እንዳይላኩ በተለያየ ጊዜ ከሚመለከታቸው ጋራ ንግግር እያደረግን ነው አሁንም ችግሩን ለማስቀረት የቻልነውን ጥረት እናደርጋለን’’ም ብለዋል፡፡


ከሙቀት በተጨማሪ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች፣ በየመንገዱ በታጣቂዎች ግድያ እንደሚፈጸምባቸው ማህበሩ አስታውሷል፡፡



ማንያዘዋል ጌታሁን

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page