top of page

ነሐሴ 16፣2016 - በፕሪቶሪያው የሰለም ስምምነት የፌደራል መንግስት ለህውሃት ለመፈፀም የገባው ስምምነት ምንድነው?

የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ሕወሃት) በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የቀድሞ ህጋዊ ሰውነቴ ይመለስልኝ ሲል፤ መንግስት በበኩሉ የሕወሃትን የህግ ሰውነት እና ምዝገባ ጉዳይ በስምምነቱ ውስጥ የወሰድኩት የተለየ ኃላፊነት አልያም ግዴታ የለም ብሏል፡፡


ሕወሃት በበኩሉ ስምምነቱ እንዲህ ባለ መልኩ መተረጎም የለበትም ብሏል፡፡


ይህም በሁለት በተከፈለው #ህወሃት እና በፌደራል መንግስት መካከል አለመስማማትን የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል፡፡


በፕሪቶሪያው የሰለም ስምምነት ሲፈረም የፌደራል መንግስት የወሰደው ግዴታ የህወሃት የሽብርተኝነት ፍርድ እንዲነሳ ሂደቱን ቀና ማድረግ እንደሆነ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ተናግሯል፡፡


ከቀናት በፊት የወጣው የአገልግሎቱ መግለጫ በስምምነቱ ህወሃትም የሀገሪቱን ህገ መንግስት፣ ህጎች የፌደራል ተቋማትን እና ሌሎች ህገ መንግስታዊ ተቋማትን ስልጣን የማክበር ግዴታ መቀበሉን ተናግሯል፡፡


በዚህም መሰረት ህወሃት #ምርጫ_ቦርድ በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገብ የሳለፈውን ውሳኔ መከበር አለበት ሲል ተናግሯል፡፡


በሁለት ጎራ የተከፈለው ህውሃት በበኩሉ በልዩ ሁኔታ ሳይሆን መመዝገብ የምፈልገው የቀድሞ ህጋዊ ሰውነቴ እንዲመለስልኝ ነው ሲል መልሷል፡፡


ለመሆኑ በስምምነቱ የፌደራል መንግስት ለህውሃት ለመፈፀም የገባው ስምምነት ምንድነው?


የህግ በለሞያ የሆኑት አሮን ደጎል ‘’መንግስት የህውሃትን የቀድሞ ሰውነት ለመመለስ ሳይሆን የተስማማው የሽብርተኝነት ፍርድ አንዲነሳለት ማመቻቸት ነው’’ ይላሉ፡፡


በእነደብረጽዮን ጎራ ተደርጎ በነበረው #ጉባኤ በጌታቸው ረዳን በመተካት የህወሃት ምክትል ሊቀመንበር ተደርገው የተመረጡት አማኑኤል አሰፋ ስምምነቱ እንዲህ ባለ መልኩ መተረጎም የለበትም ይላሉ፡፡


አቶ አማኑኤል ‘’በፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ በግልጽ የተቀመጠው ሁለቱም አካላት በቀና ልቦና በቅንነት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ይፈጽማሉ ነው የሚለው’’ ብለዋል፡፡


‘’የፕሪቶሪያውን ስምምነት ይፈጸማል ከተባለ የሆነ መንገድ ላይ ሄደው አንዱ ሌላውን ለማጥፋት የሚያስችለውን ሶፍት ፓወር መጠቀም የለበትም ይሄ በሶፍት ፓወር ህውሃትን የማጥፋት ጉዞ ነው ይህ አካሄድ ለሰላም አይጠቅምም’’ ሲሉ አስረድተዋል፡፡



ያሬድ እንዳሻው

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page