top of page

ነሐሴ 15፣2016 - አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የመልሶ ግንባታ እያከናወንኩ ቢሆንም ፈተናዎች ይገጥሙኛል ሲል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተናገረ

  • sheger1021fm
  • Aug 21, 2024
  • 2 min read

በሰላም እጦትም ሆነ በስርቆት ምክንያት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የመልሶ ግንባታ እያከናወንኩ ቢሆንም ፈተናዎች ይገጥሙኛል ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተናገረ፡፡


በተለያዩ ምክንያቶች ከጥቅም ውጭ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመጠገን ስራ እየከወንኩ ነው ያለው ተቋሙ አገልግሎቱን ወደ ነበረበት ለለመመለስ የማወጣው ወጭ አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን ይከውንልኝ ነበር ብሏል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚፈጠረው የሰላም እጦት በመሰረተ ልማቶቹ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ያሉት የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በስርቆት ምክንያትም ችግር የደረሰባቸው መሰረተ ልማቶች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡


ከአራት እስከ ስድስት ለአመታት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ መሰረተ ልማቶች መኖራቸውም የተነገረ ሲሆን እነሱን በመጠገን አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራ እየተከወነ ነው መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡


በጦርነቱም ምክንያት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ምሰሶዎች እና ትራንስፎርመሮች ጉዳት እንደደረሰባቸው ሲናገሩ ሰምተናል፡፡


በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ለአመታት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ መሰረተ ልማቶችንም የመጠገን ስራ እየከወንን ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ እና ትግራይ እልሎች መሰል ስራዎችን ሰርተናል ብለዋል፡፡


አሁን ደግሞ በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ባሉ ወረዳዎች ለአራት ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የአሌክትሪክ መሰረተ ልማት የመልሶ ግንባታ እያከናወነ እንደሚገኝ አቶ መላኩ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡

የመልሶ ግንባታውንም ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል የተባለ ሲሆን ከዚህ ቀደም በዞኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የማይጠቀሙ አካባቢዎችንም እግረ መንገዴን አገልግሎቱን እንዲያገኙ እያረኩ ነው ብሏል፡፡


የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኦሮሚያ ክልል አራቱም የወለጋ ዞኖች በተከሰተው የፀጥታ ችግር ለስድስት ዓመታት ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጭ የነበሩ 143 ከተሞች እና ቀበሌዎች የመልሶ ግንባታ ማከናወኑን ተናግሯል፡፡


በተከናወነው የመልሶ ጥገና ስራ በምስራቅ ወለጋ ዞን 53 አካባቢዎች፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን 36 ቀበሌዎች፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን 35 አካባቢዎች እሀንዲሁም በቄለም ወለጋ ዞን 19 ቀበሌዎች በአጠቃላይ 143 የገጠር ቀበሌዎች እና ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጌአለሁ ብሏል አገልግሎቱ፡፡


ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከማያገኙ አካባቢዎች መካከል 100 የገጠር ቀበሌዎችን እና ከተሞችን የአገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ እንደነበር የተናገረው አገልግሎቱ በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት 116 ለሚሆኑ አካባቢዎች አዲስ የመሰረተ ልማት ዝርጋ አከናውኛለሁ ብሏል፡፡



ፋሲካ ሙሉወርቅ

Kommentarer


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page