የከተማው በጎ ፍቃደኛ የሰላም ሰራዊቶች ምሽት ላይ ሌባ ነው ብለው ከያዙት እና ያለ መታወቂያ ከሚንቀሳቀስ ሰው ስልክን ጨምሮ የያዘውን ነጥቅው ለራሳቸው የሚያደርጉ አሉ ተባለ፡፡
ይህን ያሉት ሸገር የነጋገራቸው በጎ ፍቃደኛ አካባቢ ጠባቂዎች ወይም በተለምዶ ‘’የሰላም ሰራዊት’’ የሚል መጠሪያ ያላቸው ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በበኩሉ ‘’የሥነ ምግባር ችግር አለባቸው ብዬ አላስብም ካለም እርምጃ እወስዳለው’’ ብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በተለምዶ የሰላም ሰራዊት የሚል መጠሪያ ያላቸውን በጎ ፍቃደኛ የአካባቢ ጠባቂዎች ቁጥር 241,000 ማድረሱንም ተናግሯል፡፡
እነዚህ በጎ ፍቃደኞች ምሽት ላይ አንጸባራቂ በመልበስ አካባቢዎቻቸውን ‘’ከፀጉረ ልውጥ ሰዎች እና ከሌቦች የሚጠብቁ ናቸው’’ ተብሏል፡፡

ታዲያ በእነዚህ አካባቢ ጠባቂዎች ላይ ማህበረሰቡ የተለያየ ቅሬታዎችን እንደሚያነሳባቸው ሸገር ከበጎ ፍቃደኞቹ ሰምቷል፡፡
በጎ ፍቃደኞቹ ‘’ይህ አደረጃጃት ከተፈጠረ ወዲህ ሌብነትን ጨምሮ የደረቅ ወንጀል የቀነሰ ቢሆንም አንዳንዶች ምሽት ላይ የያዙትን የተለያየ ንብረት ለፖሊስ ማስረከብ ሲገባቸው ለግላቸው የሚደርጉ የስነ-ምግባር ጉድለት ያለባቸው አሉ’’ ብለዋል፡፡
‘’ድንገት መታወቂያ ሳይዝ የወጣን ሰው ያንገላታሉ፣ መብቱን የሚጠይቀውን ደግሞ ይደበድባሉ ሌባ ነው ብለው የያዙትን ደግሞ ስልኩን እና ንብረቱን ለፖሊስ ከማስረከብ ይልቅ ለራሳቸው ይወስዳሉ’’ የሚሉ ይገኙበታል፡፡

በተለምዶ የሰላም ሰራዊት የሚል መጠሪያ ያላቸው በጎ ፍቃደኛ የአካባቢ ጠባቂዎችም ሌባ ነው ብለው ከያዙት ግለሰብም ይሁን ቡድን የያዘውን ስልክም ይሁን ንብረት ቀምተው ለራሳቸው የሚደርጉ መኖራቸውን ነግረውናል፡፡
የሰላም ሰራዊት የሚል መጠሪያ ያለቸው በጎ ፍቃደኛ የአካባቢ ጠባቂዎችን የሚያምኗቸው ኗሪዎች እንዳሉ ሁሉ ‘’የመንግስት ጆሮ ጠቢ፣ የፓርቲ ጉዳይ ፈጻሚ’’ የሚል መጠሪያ ሰጥተዋቸው የማያምኗቸው እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሚደቅሳ ከበደ ‘’የሰላም ሰራዊት የተደራጀው በህልውናው ዘመቻ ወቅት በመሆኑ ቀድመው በተደራጁት ላይ ችግሩ ሊኖር ይችላል አሁን ባሉት ላይ የስነ-ምግባር ችግር አለ ብለን አናንም ካለም እርምጃ እንወስዳለን’’ ብለዋል፡፡

አሁን ያለው ‘’በጣም የተደራጀ የተሻለ ስብእና ያለው ሃይል ስብስብ ነው’’ ያሉት ምክትል ሃላፊው ብዙ የቀረበ ቅሬታ እና ወጣ ያሉ ድርጊቶች የሉም የትኛው አካል ህግን ተከትሎ ካልሰራ ግን ተጠያቂ ይደረጋል’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ ሚደቅሳ የማያምናቸው ህዝብ አለ ለሚለው ጥያቄም ‘’የሰላም ሰራዊቱ የህዝብ አካል ነው ከህዝብ ነጥለን የምናየው ሃይል አይደለም ተከፋይም አይደለም ሰላም ፈላጊ የከተማዋ ኗሪ አቅም ያለው በአቅሙ ጉልበት ያለው በጉልበቱ አካባቢውን ወረዳውን ለመጠበቅ የተቋቋመ ነው፤ በማህበረሰቡ ከፍተኛ ቅቡልነት ያለው ኃይል ነው’’ ሲሉ መልሰዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን በድምፅ ለማድመጥ ይህንን ይጫኑ...
ያሬድ እንዳሻው
Comments