ከክልል አደረጃጀት ጋር በተያያዘ መብታቸውን ለመጠየቅ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ዜጎች ያላግባብ እየታሰሩ ነው ሲል የጋሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /ጋዲፓ/ ተናገረ፡፡
የጋሞ ሕዝብ ጥያቄ ታፍኗል ሲል የጋሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲው ወቅሷል፡፡
ፓርቲው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝቡን ጥያቄ አፍኗል ያለው በትናንትናው እለት ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ነው፡፡
የጋሞ ህዝብ ህገ-መንግስቱ በሚፈቅደው አሰራር የክልልነት ጥያቄ ቢጠይቅም ምክር ቤቱ የህዝቡን ጥያቄ አፍኖ የራሱን ውሳኔ ወስኗል ሲል በመግለጫው ተናግሯል፡፡
በቅርቡ የተደረገው ህዝበ ውሳኔም የጋሞን ሕዝብ ያላማከለ እና ያላማከረ ውሳኔ ነው ብሏል፡፡
በፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ዳሮት ጉመአ የጋሞን ሕዝብ የጠየቀው ሕገ መንግስታዊ መብቱ እንዲመለስለት እንሻለን ሲሉ ሰምተናል፡፡
ህገ መንግስቱ መስፈርቱን ላሟሉ በክልል እንዲደራጁ ቢፈቅድም የጋሞ ዞን ምክር ቤት ዞኑ በክልልነት እንዲደራጅ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀው ውሳኔ ታፍኗል ብለዋል ምክትል ሊቀመንበሩ፡፡
የጋሞ ህዝብ በክልል እንዲደራጅ ከዞኑ ምክር ቤት ሙሉ ድምፅ ቢያገኝም የአገሪቱ ቁንጮ የሆነውን ህገ-መንግስት የቸረንን መብት ተነፍገናል ሲሉ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ከሰዋል፡፡
የዞኑ ምክር ቤቱ በተዘረጋው አሰራር መሰረት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረቡ የተናገረው ፓርቲው ምላሽ አላገኘም ብሏል፡፡
የአሁኑ አስተዳደርም የህዝቡን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ጥያቄ የሚያነሱ ወጣቶችን እያሰረና የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈፀመባቸው ነው ብለዋል፡፡
ባለፈው ነሐሴ 4 ቀን 2015 ዓ.ም የክልሉ ነዋሪዎች በቅርቡ የተወሰነውን አዲሱን አደረጀጃት ለመቃወምና ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠየቅ ሰልፍ ከወጡ ሰዎች የታሰሩ ብዛትም ከ400 በላይ መሆናቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
ፓርቲው ትናንት በሰጠው መግለጫ የጋሞ ዞን አርባ ምርንጭን ማዕከል ያደረገ ጋሞ ብሔራዊ ክልል እንዲቋቋም መጠየቁን ሰምተናል፡፡
ያሬድ እንዳሻው

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website: t.ly/ShegerFM
YouTube: t.ly/SHEGER
Comentarios