top of page

ነሀሴ 7 2017 - ህግ ተላልፈዋል ያላቸውን ከ14,000 በላይ ግብር ከፋዮች በገንዘብ መቅጣቱን የገቢዎች ቢሮ ተናገረ

  • sheger1021fm
  • Aug 13
  • 2 min read

ህግ ተላልፈዋል ያላቸውን ከ14,000 በላይ ግብር ከፋዮች በገንዘብ መቅጣቱን የገቢዎች ቢሮ ተናገረ።


የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ይህንን ያለው የግብር አሰባሰቡን ከሌብነት የፀዳ ለማድረግ ያግዙኛል ያላቸውን ቴክኖሎጂዎች ባስተዋወቀበት መድረክ ነው።


በዚህም የግብር ህጉን ተላላፈዋል የተባሉ 14,220 ግብር ከፋዮች 763,675,000 ብር ተቀጥተዋል ተብሏል።


በገንዘብ ከተቀጡ ግብር ከፋዮች ገሚሱ ማለትም 7,701 ያህሉ ደረሰኝ ባለመቁረጥ እያንዳንዳቸው 100,000 ብር የተቀጡ መሆናቸው ተጠቅሷል።


ቀሪዎቹ ደግሞ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ባለማደስ፣ ማስታወቂያ ባለመለጠፍ፣ ማሽን ያለ ያለቦታው በማስቀመጥ፣ ለቁጥጥር ባለሙያዎች መረጃ ለመስጠት ባለመተባበር የተቀጡ መሆኑን ቢሮው ተናግሯል።


በመርካቶ አካባቢ የሚደረገውን የገቢ አሰባሰብ በቴክኖሎጂ ለማገዝ በማሰብ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን አሰራር ተዘርግቷል ተብሏል።

ree

የቢሮው የቁጥጥር ባለሙያዎቹ ማንነታቸውን የሚገልፅ ኮድ የያዘ የደምብ ልብስ በመልበስና በኪው አር ኮድ ስካን የሚደረግ መታወቂያ መበያዝ ስራቸውን እንደሚሰሩ የቢሮው ምክትል ሃላፊና የታክስ ዘርፍ ሃላፊዋ ወ/ሮ ወርቅነሽ ሰቦቃ ነግረውናል።


አሰራሩን መቀየር ያስፈለገው አንዳንድ የቁጥጥር ባለሙያዎች በተለይ በመርካቶ አካባቢ የተሰጣቸውን ሃላፊነት ወደጎን በመተው ከግብር ከፋዩ ጋር በጥቅም የሚደራደሩ በመኖራቸው ይህንን ለማስቀረት መሆኑንም አንስተዋል።


ከዚህም ባሻገር ከገቢዎች ነው የመጣነው በሚል የሚያጭበረብሩ ግለሰቦች በመኖራቸው፤ ይህንን ለመከላከል የተደረገ ነው ብለዋል።


ከዚህ በኋላ በተለይ አሰራሩ በተጀመረባቸው የመርካቶና አዲስ ከተማ ግብር ከፋዮች ማንኛውም ከገቢዎች ቢሮ ነው የመጣሁት የሚላችሁን ግለሰብ ማንነት በለበሰው ኮድ ያለበት የደምብ ልብስ እንድታረጋግጡ፤ እንዲሁም የያዘው የዲጂታል መታወቂያ ላይ የሚገኘውን ኪው አር ኮድ በስልካችሁ ስካን በማድረግ እንድታረጋግጡ ተብላችኋል።


በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ተገቢውን አገልግሎት ባለመስጠት ችግር ፈጥረዋል የተባሉ ከ200 በላይ የገቢ ሰብሳቢው መስሪያ ቤት ሰራተኞች ከስራ ከማሰናበት ለህግ እስከማቅረብ የደረሰ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ተብሏል፡፡


በዓመቱ ተገልጋዩን ማህበረሰብ በማንጉላላት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ችግር ፈጥረዋል የተባሉ ሰራተኞች ላይ ከስራ እስከ ማሰናበት የደረሰ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል፡፡


እንዲሁም እጅ መንሻ ሲቀበሉ የተደረሰባቸው ደግሞ ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በህግ እየታየ ይገኛል፡፡


አዲስ አበባ በመጪው የ2018 ዓ.ም በከተማ ደረጃ 350 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ውጥን ይዛለች።


ከዚህ ውስጥ የገቢ ሰብሳቢው መስሪያ ቤት 256 ቢሊዮን ብሩን እንደሚሰበስብ ከቢሮው የታክስ ዘርፍ ሃላፊ ከወ/ሮ ወርቆነሽ ሰቦቃ ሰምተናል።


ይህንን ውጥን ለማሳካትም 24 የሚደርሱ አዳዲስ አሰራሮችን በጥናት በመለየት ወደ ስራ ገብቷልም ተብሏል።


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page