ነሀሴ 6 2017 - በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በኢትዮጵያ የሙቀት መጠን በየዓመቱ በአማካይ ከ1 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እየጨመረ ነው ተባለ፡፡
- sheger1021fm
- Aug 12
- 2 min read
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በኢትዮጵያ የሙቀት መጠን በየዓመቱ በአማካይ ከ1 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እየጨመረ ነው ተባለ፡፡
ኢትዮጵያ ከአለም ሀገራት ያላት የ #በካይ_ጋዝ ልቀት ድርሻ ግን 0.04 በመቶ ነው ተብሏል፡፡
ያደጉት ሀገራት ለአፍሪካ በየጉባኤው ቃል የሚገቡትን የአየር ንብረት ለውጥ መደገፊያ የፋይናንስ ድጋፍ እየሰጡ ስላልሆነ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የሚሰራው ስራ የሚፈለገውን ያህል መሆን አልቻለም ተብሏል፡፡

ይህ የተነገረው በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚመክረውና ኢትዮጵያ ከጳጉሜ 3 እስከ 5 ከምታሰናዳው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አስቀድሞ በተሰናዳ ዝግጅት ላይ ነው፡፡
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዛሬ ያሰናዳውና ነገም የሚቀጥለው ጉባኤና ኢግዚብሽን ከዋናው ጉባኤ በፊት የሚደረግ ቅድመ ጉባኤ ስለመሆኑ ተናግሯል፡፡
በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታው ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ እና በአለም ዙሪያ ተፅዕኖ ደጋግሞ መታየት እየጀመረ ነው ብለዋል፡፡
ይህም ተፅዕኖ ባለፉት አመታት በኢትዮጵያ የሙቀት መጠኑ በየአመቱ በአማካይ ከ1 እስከ 1.5 ዲግሪ ሼልሲየሽ እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በግብርና ምርት ላይ ጥገኛ በመሆኑ የአፍሪካ ሀገራት የዝናብ መጠን መዛባትና ወጥነት የሌለው ሥርጭት እየታየ የግብርና ስራቸውን እየፈተነ ነው ብለዋል፡፡
በየአካባቢው በ10 ዓመትና ከዚያም በላይ ሊከሰት የነበረው የጎርፍ አደጋ አሁን ደጋግሞ የሚታይና ከፍተኛ ጉዳትም የሚያደርስ እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡
የተራዘመና ተደጋጋሚ ድርቅ በየአካባቢው መታየት ከፍተኛ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር የውሃ እጥረት መከሰት እንደ ወባ ያሉ የጤና ችግሮች መጠናቸው መጨመር እና ሌሎችም ደጋግመው እየታዩ ያሉ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ውጤት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህ ሁሉ ተፅዕኖ በኢትዮጵያም በስፋት እየታየ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዲኤታው በአለም የበካይ ጋዝ ወይም የካርበር ልቀት የኢትዮጵያ ድርሻ ግን 0.04 በመቶ ነው ብለዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ ያስረዳው አሁንም በአለም ዙሪያ 82 በመቶ የሀይል ፍላጎት እየተሸፈ ያለው እንደ ነዳጅና የድንጋይ ከሰል ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ድርሻ በሚወስደው የሀይል አማራጭ ነው፡፡
በሌላ በኩል በአለም ዙሪያ የታዳሽ ሀይል የመጠቀም እድገቱ 2 በመቶ ብቻ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ሚኒስትር ዲኤታው ኢንጂነር ሱልጣን እንዳሉት ኢትዮጵያ በምታሰናዳው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የአፍሪካ አማራጭ የአየር ንብረት መከላከያ መንገዶችና ቴክኖሎጂዎችን ለቀረው አለም ለማስተዋወቅ አፍሪካ በአንድነት መቆም ይኖርባታል፡፡
ቃል የሚገባው የአየር ንብረት ለውጥ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ተግባራዊ እንዲሆንም አፍሪካዊያን ጥያቄ ያቀርቡበታል ብለዋል፡፡
ቴዎድሮስ ወርቁ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments