top of page

ነሀሴ 19 2017 - በኦሞ ወንዝና በቱርካና ሃይቅ መሙላት ምክንያት የመዋጥ አደጋ ላይ ያለችው የኦሞራቴ ከተማ

  • sheger1021fm
  • Aug 25
  • 1 min read

በኦሞ ወንዝና በቱርካና ሃይቅ መሙላት ምክንያት የመዋጥ አደጋ ላይ ያለችው የኦሞራቴ ከተማ ታሪክ ልትሆን ተቃርባለች ተባለ፡፡


የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ የሆነች የኦሞራቴ ከተማ ከዓመት ዓመት በቱርካና ሃይቅ እና በኦሞ ወንዝ መሙላት ምክንያት የመዋጥ ስጋት እንዳለባት ሲነገር ቆይቷል፡፡


ከተማዋን የተጠጋት ውሃ ዘልቆ እንዳይገባ ጊዜያዊ መከላከያ ግድብ ቢሰራም ውሃው በከፍተኛ መጠን እየመጣ በመሆቡ ግድቡን ጥሶ ከተማዋን እንዳያጥለቀልቃት ስጋት ውስጥ ነን ያሉን የዞኑ አደጋ ስጋት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኞክ ኛንጋ ሞሮኜ ናቸው፡፡


በ2017 ዓ/ም መጀመሪያ የመስከረም ወር አካባቢ በአቅራቢያ ያሉ የደቡብ ኦሞ ወረዳዎችን ውጦ በማስቀረት ወደ ዋና ከተማዋ ኦሞራቴ ለመድረስ የ1.5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የነበረው የቱርካና ሃይቅ ሙላት አሁን በጥቂት መቶ ሜትሮች ላይ ነው ያለው ተብሏል፡፡


ይህ ሁሉ ሲሆን ከፌድራሉ መንግስት ድጋፍ አልጠየቃችሁም ወይ?ያልናቸው ምክትል ሃላፊው፤ ለፌዴራሉ መንግስት በተለይ ለአደጋ ስጋት መስሪያ ቤት በተደጋጋሚ አሳውቀናል፤ ነዋሪውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጥተው ያሉበትን ችግር እንዲያዩ ጥሪ አድርጓል ነገር ግን ይህ ነው የሚባል ምላሽ አላገኘንም ብለዋል፡፡


ባለፈው ዓመት በነበረው መጥለቅለቅ ከአካባቢያቸው የለቀቁ ከ81,000 በላይ ነዋሪዎችን ደረቅ በሆኑ ቦታዎች አስፍረን ድጋፍ እያደረግንላቸው ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡


የውሃው ሙላት በዚህ ቀጥሎ የተሰራውን መገደቢያ የሚያፈርስ ከሆነ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠረውን የኦሞራቴ ከተማ ነዋሪ ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር እየተዘጋጁ መሆኑን ከሃላፊው ሰምተናል፡፡


የፌድራሉ መንግስት ችግሩን እንዲመለከተውና መፍትሄ እንዲሰጣቸው የጠየቁት ሃላፊው እያደረግን ያለነው ሙከራ ከአቅማችን በላይ እየሆነ ነው አቅማችን ተሟጧል ከተማችን ሳትጠፋ ድረሱልን ብለዋል፡፡


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page