ነሀሴ 13 2017 - በኢትዮጵያ የደጋ አጋዘን ለማደን 15,000 ዶላር ያስከፍላል፤ ይህም ከፍተኛው የዱር እንስሳት የማደኛ ዋጋ ነው ተባለ
- sheger1021fm
- Aug 19
- 1 min read
በኢትዮጵያ የደጋ አጋዘን ለማደን 15,000 ዶላር ያስከፍላል፤ ይህም ከፍተኛው የዱር እንስሳት የማደኛ ዋጋ ነው ተባለ፡፡
አንበሳን የሚያድን ሰው 4,000 ዶላር ፣ ነብር 4,600 ዶላር ይታደናል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት ከዱር እንስሳት ህጋዊ አደን 193 ሚልየን ብር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ተናገረ፡፡
በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ የታቀደው 200 ሚልየን ብር ነበር፡፡
ሀገሪቱ ካላት የዱር እንስሳት ሀብቷ መካከል 54 የሚሆኑትን #ህጋዊ_አደን እንዲፈጸምባቸው ትፈቅዳለች፡፡
እንደ ዝሆን፣ ዋልያ፣ አቦሸማኔ እና ቀጭኔን ጨምሮ 48 የዱር እንስሳት ደግሞ ለአደን የተከለከሉ ናቸው፡፡
በዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የዱር እስሳት አጠቃቀም ዴስክ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ወርቁ የውጪ ሀገር አዳኝ ቱሪስቶች ወደ ሀገር ቤት ለአደን ከመጡ በኋላ የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ለማድረግ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት ጥበቃና አጠቃቀምን በተመለከተ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው ደንብ ባስቀመጠው መሰረት አነስተኛው የማደኛ ዋጋ የጥርኝ ሲሆን 15 ዶላር፣ የጃርትን ደግሞ 20 ዶላር ያስከፍላል፡፡
የአየር ፊልም ቀረፃን ለማድረግ 15,000 ዶላር የሚያስከፍል ሲሆን በመሬት ቀረፃ ለማድረግ 9,000 ዶላር ይጠይቃል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ማደን የሚቻለው ያረጁ ወንድ የዱር እንስሳ ብቻ ነው ያሉን አቶ ዳንኤል ወርቁ ሴቶችና ወጣት ወንድ የዱር እንስሳት ማደን የተከለከለ ነው ብለዋል፡፡
የተከለከሉ የዱር እንስሳትን ያደነ ሰው የተቀመጠውን የማደኛ ዋጋ እጥፍ ይከፍላል ተብሏል፡፡
አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ህጋዊ የዱር እንስሳት አደን ይካሄዳል፡፡
የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ከነባሮቹ በተጨማሪ አዳዲስ ህጋዊ የማደኛ ስፍራዎችን ለመክፈት እየሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በረከት አካሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments