ነሀሴ 1 2017 - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ካመነጨሁት ሀይል 33.2 በመቶው የተገኘው ከህዳሴ ግድቡ ነው አለ።
- sheger1021fm
- Aug 7
- 1 min read
በበጀት ዓመቱ ከተገኘው ሀይል 93 በመቶው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የተቀረው 7 በመቶ ደግሞ ለውጪ ሀገራት የተሸጠ መሆኑ ተነግሯል።
ተቋሙ ይህንን ያለው የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀሙን እና የ2018 በጀት ዓመት እቅዱን በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ነው።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 29,480 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨቱን ተናግሯል።
ይህም ካቀድኩት በላይ ነው ያለው ተቋሙ በበጀት ዓመቱ 25,423 ጊጋ ዋት ሰዓት የማምረት እቅድ ነው የነበረኝ ብሏል።
ከሀይል ሽያጩ 75.4 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ ተናግረዋል።

ከመነጨው ሀይልም 33.2 በመቶው የተገኘው ከህዳሴ ግድቡ መሆኑን ያብራሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው ኢንጅነር አሸብር ባልቻ 93 በመቶው የመነጨው ሀይል ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የተቀረው 7 በመቶ ደግሞ ለውጭ ሀገራት የተሸጠ ነው ብለዋል።
ለሀገር ውስጥ ከቀረበው 93 በመቶ ሀይል 60 በመቶው ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተሸጠ፣ 27 በመቶው ለዳታ ማይኒንግ እና 6 በመቶው ደግሞ ለኢንዱስትሪዎች የተሸጠ መሆኑን ከተቋሙ ሰምተናል።
ከአጠቃላይ የመነጨ ሀይል 7 በመቶው ለውጭ ሽያጭ መቅረቡን ያስረዱት ሀላፊው ለውጭ ሀገራት በሽያጭ ከቀረበው 5 በመቶው ለኬኒያ እና 2 በመቶው ለጅቡቲ እንደተሸጠ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል በተጠናቀቀው በጀት አመት ችግር ሆነውብኛል ስላላቸው ጉዳዮችም አንስቷል።
የመሰረተ ልማት ስርቆት ሲፈትነኝ ቆይቷል ያለው ተቋሙ፤በ43 የሀይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በተፈፀመ ስርቆት ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶብኛል ብሏል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው የሰላም እጦት እንደልብ ስራዎችን ተዘዋውሬ መስራት እንዳልችል ያደረገኝ ሌላኛው ችግር ነው ሲል ተናግሯል።
ፋሲካ ሙሉወርቅ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyu.com/ycxjmm3s












Comments