ቻይና የኢትዮጵያ ቡና 3ኛዋ ትልቅ ገዥ ሆነች።
- Jun 18
- 1 min read
ሰኔ 11/2018
ቻይና የኢትዮጵያ ቡና 3ኛዋ ትልቅ ገዥ ሆነች።
2ኛው የጋራ የቡና ኤግዚቢሽንም ሊካሄድ ነው መሆኑን የቡናና ሻይ ባለስልጣን ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከፍተኛ አመራሮች ‹ጁጆ ሎጂስቲክስ› ከተባለው የቻይና ኩባንያ ተወካዮች ጋር በዋና መስሪያ ቤታቸው ተቀብለው ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም የሁለቱ ሀገራት የቡና ንግድ ትስስር እያሳየ የመጣው ከፍተኛ ዕድገትና ቀጣይ የትብብር ዕድሎች ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል።

የቻይናው ኩባንያ ተወካዮች ባሳለፍነው ዓመት የመጀመሪያው የኢትዮ-ቻይና የቡና ኤግዚቢሽን በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን አስታውሰዋል።
በወቅቱ የኢትዮጵያ ባህላዊ የቡና አፈላል ሥነ-ሥርዓት ቀርቦ ምርቱን የማስተዋወቅ ትልቅ ሥራ መሠራቱን የጠቀሱት ተወካዮቹ፣ በዕለቱም የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር ) ተገኝተው እንደነበር ጠቅሰዋል።
2ኛው የኢትዮ-ቻይና የቡና ኤግዚቢሽን በመጪው መስከረም 15 ቀን እንደሚካሄድ ተነግሯል።
በመጀመሪያው ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያ የቡና ዘርፍ ተዋናዮች ተሳትፎ አነስተኛ እንደነበር አንስተዋል።

በመሆኑም በዘንድሮው ሁለተኛ ዙር ዝግጅት ላይ የሀገሪቱ የቡና ላኪዎች፣ አምራቾችና መላው የቡናው ማኅበረሰብ በስፋትና በበቂ ሁኔታ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የቡናና ሻይ አመራሮች በበኩላቸው ቻይና ለኢትዮጵያ ቡና ለሰጠችው ከፍተኛ ቦታና ለምታደርገው የማስተዋወቅ ሥራ አድንቀዋል።
በሁለተኛው ኤግዚቢሽን ላይ ባለስልጣኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና የሀገር ውስጥ የቡና ተዋናዮች በስፋት እንዲሳተፉ የበኩሉን የቅስቀሳ ሚና እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት 7ኛ ደረጃ ላይ የነበረችው ቻይና፣ ዘንድሮ 3ኛ ደረጃ ላይ መገኘቷ ተጠቅሷል።
ንጋቱ ሙሉ





Comments