ታሪክን የኋሊት - ሚያዝያ 8፣2017 - ፊደል ካስትሮ
- sheger1021fm
- Apr 16
- 2 min read
የቀድሞው የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮ በግራ ክንፈኛ ሸምቅ ተዋጊነታቸው ይታወቃሉ፡፡
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የዘመኑ የጄኔራል ባቲስታ አስተዳደር ጨቋኝና አምባገነን ነው ባሉ ጊዜ የሽምቅ ውጊያ ቡድን አቋቋሙ፡፡
ከብረት ጓዶቻቸው ጋር 80 ሆነውም ግራንማ በተሠኘችዋ ጀልባ ከሜክሲኮ ወደ ኩባ ቀዘፉ፡፡
አብዛኞቹ በጠረፍ ጠባቂ ወታደሮች ተረፈረፉ፡፡
የተረፉት ጥቂቶች ደግሞ እግር ወዳመራቸው ተበታተኑ፡፡
የተበታተኑት የካስትሮ ጓዶች በሴራ ሜይስትራ ተራራ ተሰባሰቡ፡፡
ተራራውን የሙጥኝ ብለው የጄኔራል ባቲስታን ጦር ይፈታተኑት ያዙ፡፡
የካስትሮ ተዋጊዎች ኃይላችው እያደረጁና እያፈረጠሙ መጡ፡፡
የባቲስታን ወታደራዊ ኃይል አንኮታኮቱት፡፡
አማፂያኑ መንግስት ሆኑ፡፡

የኮሚኒስት ሥርዓት ተከታዮች ነን ያሉት የዛሬ 64 አመት ነው፡፡
አሜሪካ የሷ ቡራኬ የነበረው የጄኔራል ባቲስታ መንግስት መውደቁ አስኮረፋት፡፡
ከደቡባዊ ግዛቷ ብዙም ባልራቀ ስፍራ ግራ ክንፈኛ መንግስት ማየቱን አልፈቀደችም፡፡
በግዛቷ የሚኖሩ ኩባውያንን በጦር አሠልጥናና አስታጥቃ የካስትሮን መንግስት ገልብጡ ብላ ላከቻቸው፡፡
በሺህዎች የሚቆጠሩ ኩባውያን ፀረ ካስትሮ ተዋጊዎችን ጓቴማላ ውስጥ በተጠንቀቅ እንዲቆዩ አደረገች፡፡
ጓቴማላ ውስጥ የሠፈሩት ፀረ ካስትሮ ኩባውያን ተዋጊዎች ካስትሮ ከጓዶቻቸው ጋር ከሜክሲኮ ወደ ኩባ በጀልባ እንደቀዘፉት ሁሉ እነሱም እንደዛ አደረጉ፡፡
በአሜሪካው ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት /ሲ.አይ.ኤ/ የሚታዘዙትና የዋሸንግተን አስተዳደር ቡራኬ የተሠጣቸው ፀረ- ካስትሮ ተዋጊዎች በኩባ ቤይ ኦፍ ፒግስ በተባለው ቦታ ሰፈሩ፡፡
በአዲሱ መንግስት ጦር ላይ ጥቃት ከፈቱ፡፡
ጊዜያዊ የበላይነትም ጨበጡ፡፡
የበላይነታቸው ብዙም አልዘለቀ፡፡
የዛን ጊዜው የኩባ ጠቅላይ ሚኒስትር ፊደል ካስትሮ ነገሩ ቢበረታ የመከላከሉን ዘመቻ ራሳቸው መሩት፡፡
የሲ.አይ.ኤ አይዟችሁ ያላቸው ኩባውያን ታጣቂዎች በፕላያ ሂሮን ተሸነፉ፡፡ አብዛኞቹም ተማረኩ፡፡ የፕላያ ሄሮን ሸንፈት አሜሪካንን ሐፍረት ላይ ጣላት፡፡
የካስትሮ መንግስት የሞራል ከፍታው ጨመረ፡፡
የመሰል ወረራ ስጋትን ለመቀነስ ከሞስኮ ጋር ተወዳጀ፡፡
አሜሪካ በራሷ የካስትሮን መንግስት ለመገልበጥ ቀጥተኛ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለመፈፀም ማሴርና መዛቱን ገፋችበት፡፡
ይሄም አሜሪካና የቀድሞዋን ሶቪየት ህብረት ወደ ኒኩሊየር ጦርነት ፍጥጫ አድርሷቸው ነበር፡፡
ኩባና አሜሪካ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በበጐ ዓይን አይተያዩም፡፡
እሸቴ አሰፋ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
📌Spotify : https://shorturl.at/QG8f2
Comments