top of page

ታሪክን የኋሊት - ሚያዝያ 16 2017 - በኢራን ወጣቶች የታገቱባትን ዜጎቿን ለማስለቀቅ ፣ አሜሪካ የላከቻቸው ወታደሮች የግዳጅ ቀን

  • sheger1021fm
  • Apr 24
  • 2 min read

በኢራን ወጣቶች የታገቱባትን ዜጎቿን ለማስለቀቅ፣ አሜሪካ የላከቻቸው ወታደሮች ግዳጃቸው ሳይሳካ ፣ ሞትና ቁስለኛ ሆነው የተመለሱት ፣ በ1972 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡


የኢራኑ ንጉሥ ከስልጣናቸው ተባረው ከተሰደዱ በኋላ ፣ የኢራን ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በአሜሪካን ኤምባሲ ከበው ፣ በውስጡ ያሉትን ሁሉ አገቱ፡፡


ተማሪዎቹ ኤምባሲውን የከበቡት አሜሪካ ንጉሡ እንዲያመልጡ ረድታለች ብለው ነው፡፡

አዲስ የተመሰረተው እስላማዊ መንግስት መሪ የሆኑት አያቶላ ሆሚኒ እገታውን ከተማሪዎቹ ተቀብለው በርሳቸው ቁጥጥር ስር አደረጉ፡፡


የአሜሪካ ዜግነት የሌላቸውንና ሴቶችን ለቀው 52 አሜሪካውያን ግን ታግተው እንዲቆዩ አደረጉ፡፡


አሜሪካ ዜጎቿን ለማስለቀቅ የዲፕሎማሲ ጥረት ብታደርግም አልተሳካም፡፡


በስድስተኛው ወር ታጋቾችን ለማስለቀቅ ኮማንዶዎች እንዲሰማሩ ፕሬዘዳንት ካርተር ትዕዛዝ ሰጡ፡፡


የአሞራ ጥፍር በሚል የዘመቻ ስያሜ ለግዳጅ ስምንት ሄሊኮፕተሮች ከተሟላ የኮማንዶ ወታደሮችና ትጥቅ ጋር ተዘጋጁ፡፡


ሄሊኮፕተሮቹና C 130 የመጓጓዣ አይሮፕላኖች ከተለያዩ የጦር ሰፈሮች ተነስተው ከቴህራን 250 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በረሃ አንድ ብለው ከሰየሙት ቦታ ያርፋሉ፡፡

ከበረሃ አንድ በመኪና ተጓጉዘው ለቴህራን ቅርብ ወደሆነ በረሃ ሁለት ወደተባለው ቦታ እንዲሰፍሩና ምሽት ላይ ወደ ኤምባሲው እንዲደርሱ ታቀደ፡፡

ግን በግዳጅ ነጥባቸው ሳይደርሱ ሶስቱ ሄሌኮፕተሮች ተበላሹ፡፡


የብልሽቱ መነሻ ፣ የበረሃ ነፋስ ፣ የቴክኒክ ችግር ነው ተብሏል፡፡

ስለዚህ ታጋቾቹን የማስለቀቁ ግዳጅ ተሰርዞ እንዲመለሱ ታዘዙ፡፡


በመልስ ላይ እንዳሉ ፣ አንደኛው ሄሌኮፕተር ከ C 130 የወታደሮች መጓጓዣ አውሮፕላን ጋር ተላተመ፡፡


በግጭቱ ስምንት ወታደሮች ሲሞቱ አምስት ቆሰሉ፡፡


በማግስቱ ፕሬዝዳንት ካርተር በራሳቸው ድክመት የደረሰውን አደጋ ገልፀው ሙሉ ሀላፊነቱን ወሰዱ፡፡

************


ታጋቾቹን አሜሪካውያን ለማስለቀቅ አለመቻሉና ግዳጁ በራሳቸው ድክምት ባለመሳካቱ ከፍተኛ ቀውስ ቀሰቀሰ፡፡


ኢራን የታጋቾቹን ቆይታ ወደ 270 ቀናት አራዘመችው፡፡፡


ካርተር ቀጣዩን የፕሬዘዳንትነት ምርጫ እንዲሸነፉ ምክንያት ሆነባቸው፡፡

ፕሬዘዳንት ሬጋን ምርጫውን እንዳሸነፉ፣ በአልጀሪያ ሸምጋይነት አሜሪካና ኢራን ተስማሙ፡፡


ሬጋን ቃለ መሐላ በሚፈፅሙበት ቀን ኢራን ሃምሳ ሁለቱን ታጋቾች ስትለቀቅ. አሜሪካም እንዳይንቀሳቀስ አግዳው የነበረው 8 ቢሊዮን ዶላር የኢራን ገንዘብ ለቀቀች፡፡


447 ቀናት የታገቱትን አሜሪካኖች፣ ካርተር ጀርመን ድረስ ሄደው ተቀበሏቸው፡፡


በኢራን የታገቱትን አሜሪካኖች ለማስለቀቅ የተላኩት ፣ የአሜሪካ ኮማንዶዎች ያልተሳካ ግዳጅ በሞት ከተደመደመ 45 ዓመት ሆነው፡፡


እሸቴ አሰፋ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Comentários


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page