የፌደራል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በ2015 በጀት ዓመት፣ የፌደራል ዋና ኦዲተር የፋይናንስ ክዋኔ ኦዲት አካሂዶ ከህግ ውጪ ተፈፅመዋል የተባሉ የተለያዩ 27 ግኝቶች ተገኝተውበታል፡፡
ከተገኙበት የኦዲት ግኝቶች መካከል የገንዘብ ሚኒስቴር የማያውቃቸው 2 የባንክ ሂሳቦች ተከፍተው ገቢና ወጪ ሲደረግበት የነበረ ሲሆን በዚህም በበጀት ዓመቱ 87 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ሂሳብ ነበረበት ተብሏል፡፡
ይህ ሂሳብ ለ1 ዓመት ሳይንቀሳቀሰ ተቀምጧል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሚጠቀምባቸው ደረሰኞችም ቢሆን በገንዘብ ሚኒስቴር እንደማያውቃቸው በኦዲት ተረጋግጧል፡፡
በሌላበኩል 19.2 ሚልየን ብር ለአሰልጣኞች የተፈፀመ ክፍያ ሲሆን ክፍያው ወጪ ሲደረግ ህጋዊ አሰራሩ ጠብቆ የተፈጸመ አይደለም ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ለዩኒቨርሲቲው ካፌ ሰራተኞች የደመወዝ ክፍያ በሚል 563,000 ብር ያለአግባብ ወጪ ተደርጎ ተገኝቷል፡፡
136,000 ብር ደግሞ አመራሮች የትም ሳይንቀሳቀሱ አበል በሚል ስም ክፍያ መፈፀሙን የኦዲት ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
በተለያዩ የሂሳብ አርዕስቶች ለ2015 በጀት ዓመት የተደለደለ 266 ሚሊዮን ብር ስራ ላይ ሳይውል መቅረቱን የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የክዋኔ ኦዲት ግኝት እንደሚያሳይ በጉዳዩ ላይ ዛሬ በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የዩኒቨርሲቲው የስራ ሃላፊዎች ምላሽ እንዲሰጡ በተጠየቁ ጊዜ ሰምተናል፡፡
በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በ2015 በጀት ዓመት በተገኙበት 27 የኦዲት ግኝት ላይ ከስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በበጀት ዓመቱ የተገኙ የበጀት ጉድለቶችን ከላይ ከዘረዘርናቸው ግኝቶች በተጨማሪ የለአግባብ ለተማሪ ቀለብ መግዧ በሚል 20.3 ሚሊዮን ብር በበጀት ዓመቱ ወጪ የተደረገ ሲሆን በወቅቱ መወራረድ የነበረበረት ነገር ግን ሳይወራረድ የቀረ 26 ሚሊዮን ብር መገኘቱን ጠቅሷል፡፡
ከዚህ ውስጥ 1.6 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ከማን እንደሚሰበሰብ በግልፅ ማወቅ አልተቻለም ተብሏል፡፡
የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መስፍን አበበ ስለ ኦዲት ግኝት በሰጡት ምላሽ ‘’በወቅቱ ይህን ስህተት የሰራነው ባለማወቅ ነው’’ ያሉ ሲሆን ስህተት መሆኑን ካወቅን በኋላ ለማስተካከል ሞክረናል ብለዋል፡፡

ህገወጥ የተባሉት የሂሳብ ቁጥሮች አንዱን ገንዘብ ሚኒስቴር ህጋዊ እንዲያደርግልን ብንጠይቅም እስካሁን ምላሽ ሊሰጠን አልቻለም ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት መስፍን አበበ ‘’ለአሰልጣኞች የተከፈለው ክፍያ የተፈፀመው የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ተወያይቶ ካጸደቀው በኋላ ነው ህጉም ይህንን የሚፈቅድ ስለመለሰን ነው’’ ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች የሚከፈላቸው ክፍያ ተመጣጣኝ አይደለም በወቅቱ ከፍተኛ ቁጥር ሰልጣኝ መጥቶ ነበር ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሰልጣኝ ለማስተናገድ ከዚህ በፊት ተቋሙ አቅሙ አልነበረውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከአበል ክፍያ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የተገኙ የኦዲት ክፍተቶች መስተካከላቸውና የተሰጡ ክፍያዎችም እንዲመለሱ መደረጉን ኢትዮጵ ፖሊስ ዩንቨርስቲ ፕሬዳንት ተናግረዋል፡፡
ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት እና ገንዘብ ሚኒስቴር ግን በህገወጥ መንገድ የተፈጸሙ ክፍያዎች ተመላሽ ስለመደረጋቸው የደረሰን ሪፖርት የለም ብለዋል፡፡
ከህግና መመሪያ ውጪ ወጪ የተደረገው ገንዘብ እንዲመለስ እና ሌሎችም የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰድባቸው በሚል በኦዲተር መስሪያ ቤቱ በተሰጠው ምክረ ሃሳብ መሰረት እንዲስተካከል ለዩኒቨርሲቲው ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
በረከት አካሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Kommentare