top of page

ታህሳስ 8፣2017 - በቃሊቲ ማረሚያ የነበሩ ታራሚዎች አባ ሳሙኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደተገነባው ማዕከል እየተዘዋወሩ እንደሆነ ተነገረ

  • sheger1021fm
  • Dec 17, 2024
  • 1 min read

በቃሊቲ ማረሚያ ማዕከል የነበሩ የ2,200 የሚሆኑ ታራሚዎች በተለምዶ አባ ሳሙኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደተገነባው አዲስ ማዕከል እየተዘዋወሩ እንደሆነ ተነገረ፡፡


ታራሚዎቹ ወደ አዲስ ማዕከል የሚዘዋወሩት፣ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ይታዩ የነበሩት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በተሻለ ማዕከል ለመስጠት ነው ተብሏል፡፡


ለአብነትም በነባሩ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደ አዳራሽ ተደርጎ በተሰራ በአንድ ክፍል 150 ታራሚዎች ይኖሩ እንደነበረ እና በአዲሱ ማዕከል ግን በአንድ ክፍል ከ20 የማይበልጡ ታራሚዎች እንደሚሆኑም ተነግሯል፡፡


ይህንን ለሸገር ራዲዮ የነገሩት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ማዕከል አስተዳዳሪ ኮማንደር በላቸው መኮነን ናቸው፡፡


አዲሱ የታራሚዎች ማዕከል በአዲስ አበባ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እና በሸገር ከተማ አዋሳኝ ላይ የሚገኝ እንደሆነና ቀድሞ ከነበረው ማዕከልም ሩቅ የሚባል እንዳልሆነ ኮማንደር በላቸው ተናግረዋል፡፡

የታራሚዎቹን ወደ አዲሱ ማዕከል የማዘዋወር ስራ የሚከናወነውም ከዛሬ ታህሳስ 8 እስከ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ነው ተብሏል፡፡


በእነዚህ ቀናት የታራሚ ቤተሰብ ጥየቃም ሆነ የቢሮ ስራ አገልግሎት ከታህሳስ ድረስ ተቋርጦ እንደሚቆይ ተነግሯል፡፡


ለመሆኑ አዲሱ መዕከል ቀደሞ ከነበረው በምን ይለያል ስንል የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ማዕከል አስተዳዳሪ ኮማንደር በላቸው መኮነንን ጠይቀናቸዋል፡፡


አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የቃሊቲ ማረሚያ ማዕከል ቀደም ተብሎ ሲሰራም ለታራሚዎች ተብሎ አልነበረም የሚሉት ኮማንደር በላቸው በውስጡም የእስረኞች መጨናነቅ እና የተለያየ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች የነበሩበት ነው ብለዋል፡፡


በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ሁሉም ወንድ ታራሚዎች ወደ አዲሱ ማዕከል የሚዘዋሩ ሲሆን የሴቶች ማረሚያ እና ማረፊያ ማዕከል ግን እዚያው እንደሚቆይ ከማረሚያ ቤቱ ሰምተናል፡፡


ማንያዘዋል ጌታሁን ያዘጋጀውን በምህረት ስዩም


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page