በደቡብ ሱዳን ከተከሰተ ከ2 ወራት በላይ የሆነው የኮሌራ ወረርሽን የ60 ያህል ሰዎች ሕይወት ቀጠፈ ተባለ፡፡
በሀገሪቱ ከ6,000 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሌራ በሽታ እንደተያዙ በከፍተኛ መንግስታዊ ስብሰባ ወቅት መነሳቱን አናዶሉ ፅፏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የረድኤት ድርጅቶች ወረርሽኑን ለመግታት የክትባት ዘመቻ እያካሄድን ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
በተለይም የሀገር ወስጥ ተፈናቃዮች በተጠለሉባቸው ስፍራዎች የኮሌራ ወረርሽኙ አይሎባቸዋል ተብሏል፡፡
ወረርሽኑ በተለይም እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት እና ለአረጋውያን በእጅጉ አደገኛ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በሀገሪቱ የንፅህና አጠባበቅ ደረጃው ደካማ መሆን እንደኮሌራ ላሉ ወረርሽኞች መዛመት ምክንያት እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሶሪያ በጦር አሸንፈው የሀገሪቱን መንግስታዊ ስልጣን ከተቆጣጠሩት አማጺያን ጋር ግንኙነት እየፈጠርን ነው አሉ፡፡
የአሜሪካ መንግስት በሶሪያ ስልጣን ከጨበጡት አማጺያን ጋር ከጥፋተኛ ግንኙነት እየፈጠረ መሆኑን ብሊንከን ቀዳሚው ባለስልጣን እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ብሊንከን በሶሪያ እጣ ፈንታ ላይ በዮርዳኖስ ከተለያዩ የቀጠናው አገሮች ሹሞች ጋር መክረዋል ተብሏል፡፡
ሹሞቹ በሶሪያ ሽግግሩ የሰከነ እንዲሆን ፍላጎት ማሳየታቸው ተጠቅሷል፡፡
ይሁንና በዮርዳኖስ በሶሪያ ጉዳይ በመከረው ስብሰባ ላይ ስልጣን የጨበጠው የአማጺያን ጥምረት እንዳልተካፈለ ታውቋል፡፡
HTS በተሰኘው አማጺ ቡድን የሚመራው ጥምረት ተዋጊዎች የቀድሞው የሶሪያ ፕሬዘዳንት ባሻር አል አሳድ አስተዳደር ካስወገዱት ከ2 ሳምንታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡
በኮንጎ ኪንሻሣ እና በሩዋንዳ መሪዎች መካከል በአንጎላ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የሰላም ንግግር ተሰናከለ፡፡
የኮንጎ ኪንሻሣው ፕሬዘዳንት ፊሊክስ ሲሼኬዲ ለንግግሩ አልመጣም ቀረሁኝ ማለታቸውን TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡
ሁለቱ አገሮች በምስራቃዊ ኮንጎ ኪንሻሣ ብረት ካነሳ በቆየው የM-23 አማጺ ቡድን ጉዳይ ግንኙነታቸው ከደፈረሰ ቆይቷል፡፡
ኮንጎ ኪንሻሣ አማጺ ቡድኑን በአይዞህ ባይነት የምታዘምትብኝ ሩዋንዳ ነች ስትል በተደጋጋሚ ትከሳለች፡፡
ሩዋንዳ ደግሞ በኮንጎ የሚቀርብባትን ውንጀላ ታስተባብላለች፡፡
የአንጎላው የሰላም ንግግር በመክሸፉ ጉዳይ ከሩዋንዳ በኩል የተሰጠ አስተያየት የለም፡፡
በሕንድ ውቅያኖስ የፈረንሳይ የባህር ማዶ ግዛት የሆነችው ማዮት በከበደ አውሎ ነፋስ ተመታች፡፡
የአውሎ ነፋስ አደጋው በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሳይጨርስ እንዳልቀረ ተሰግቷል፡፡
የማዮት ደሴትን የመታው አውሎ ነፋስ በሰዓት 225 ኪሎ ሜትር በሆነ ፍጥነት ሲፈነጭ እንደነበር ቢቢሲ ፅፏል፡፡
አውሎ ነፋሱ የደሴቲቱን አብዛኞቹን ቤቶች ምንቅርቅራቸውን አውጥቷል ተብሏል፡፡
ደሴቲቱ የፈረንሳይ የባህር ማዶ ግዛት ብትሆንም 75 በመቶ ነዋሪዎቿ በፍጹም ድህነት ውስጥ እንደሚገኙ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ማዮት ደሴት በሞዛምቢክ እና በማዳስካር አቅራቢያ እንደምትገኝ መረጃው አስታውሷል፡፡
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments