top of page

ታህሳስ 7፣ 2015- የሕዳሴውን ግድብ በተመለከተ ኢትዮጵያ ያላትን እውነት ከማስረዳት ባለፈ ጉዳዩን የአፍሪካም አጀንዳ ልታደርገው ይገባል ተባለ

የሕዳሴውን ግድብ በተመለከተ ኢትዮጵያ ያላትን እውነት ከማስረዳት ባለፈ ጉዳዩን የአፍሪካም አጀንዳ ልታደርገው ይገባል ተባለ፡፡


ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም የዲፕሎማቲክ መንገድ የኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ የምትከተለውን አካሄድ ጊዜውን የሚመጥንና ወቅቱን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት ተብሏል፡፡


በኢትዮጵያ የውሃ ዲፕሎማሲ ዙሪያ የሚመክር ጉባኤ ዛሬ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ እየተካሄደ ነው፡፡


ጉባኤው በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስተባባሪነት እና በአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት የተሰናዳ ሲሆን ከዚህ ቀደም በአርባ ምንጭና በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ መሰል ጉባኤ ተካሄዷል፡፡


ጉባኤው ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ አጠቃቀም ዙሪያ እየሰራች ስላለችው ሥራ ለማብራራት እና ለተቀረው ዓለምም ይህንኑ በምን ዓይነት መንገድ ልታስረዳ ይገባል በሚል ሃሳብ ላይ ለመምከር የሚሰናዳ ነው ተብሏል፡፡


የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ይተፋ በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅም 90 በመቶ የሚገኘው ከውሃ ነው፡፡


ይሄም አካባቢን የማይበክልና ኃይል ለማመንጨት የምትከተለው መንገድም ሌሎችን የማይጎዳ ስለሆኑ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በልኩ ማስረዳት ይገባል ብለዋል፡፡


በየጊዜው በኢትዮጵያ የውሃ ዲፕሎማሲ ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ ጥናታዊ ፅሁፎችም በመፅሐፍ መልክ ተሰንደው በኢትዮጵያ በሚገኙ ኤምባሲዎች እንዲሁም በኦን ላየን ለተቀረው አለም እንዲደርስ ይደረጋልም ብለዋል፡፡


ዛሬ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በተከፈተው የኢትዮጵያ የውሃ ዲፕሎማሲ ጉባኤ ላይ በተመረጡ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ሀሳቦች ዙሪያ አምስት ጥናታዊ ፅሁፎች ይቀርቡበታል፡፡


ጥናታዊ ፅሁፉዎቹም በእንግሊዘኛና በአረብኛ ቋንቋ ታትመው ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲደርሱ ይደረጋል፡፡


በኢትዮጵያ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሚኒኬሽን ዙሪያ የሚመክረው ጉባኤ ለ7ኛ ጊዜ የተዘጋጀ ነው፡፡


ቴዎድሮስ ወርቁ


ሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

Comentarios


bottom of page