የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ እዝ የቀይ ባህር እና የየመን ባህረ ሰላጤን በጥንቃቄ እየተከታተልኩት ነው አለ፡፡
የየመንን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎች ከእስራኤል ጋር አንዳች ግንኙነት አላቸው ባሏቸው የንግድ መርከቦች ላይ የሚሳየል እና የድሮን ጥቃት እየሰነዘሩ ነው መባሉን አናዶሉ ፅፏል፡፡
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ እዝ የሁቲዎቹ ድርጊት በቀይ ባህር የመርከቦችን ወዲህ ወዲያ አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብሎታል፡፡
አሜሪካ በቀይ ባህር የመርከቦች ሰላማዊ ወዲህ ወዲያ እንዳይታወክ ከለላ የሚሰጥ አለም አቀፍ ጥምረት ለማቋቋም ከአጋሮቿ ጋር እየመከርኩ ነው ማለቷ ተሰምቷል፡፡
ሁቲዎቹ የእስራኤል የጋዛ ጥቃት ካልቆመ በቀይ ባህር ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች እንደሚመቱ ከዛቱ ሰንብተዋል፡፡
ሁቲዎቹ የኢራን ሁነኛ የጦር አጋሮች እና ወዳጆች መሆናቸው ይነገራል፡፡
የፍልስጤማውያኑ የጦር ድርጅት(ሐማስ) ወደ ታጋቾች እና እስረኞች ማስለቀቂያው ድርድር የምመለሰው የእስራኤል የጋዛ ጥቃት ካቆመ ብቻ ነው አለ፡፡
የእስራኤል የጋዛ ጥቃት ካልቆመ አንዳችም ንግግር አይኖርም ያሉት በሊባኖስ የሐማስ ተወካይ ኦሳማ ሐምዳን እንደሆኑ አናዶሉ ፅፏል፡፡
እስራኤል የጋዛ ዘመቻዋን የምታካሂደው ሐማስ ከ2 ወራት በፊት ወደ ደቡባዊ እስራኤል በመዝለቅ ድንገት ደራሽ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ ነው፡፡
በጊዜውም ከ240 ያላነሱ ታጋቾችን ወደ ጋዛ ይዞ መጥቷል፡፡
በፍልስጤማውያን እስረኞች መፈታት ልዋጭ የተወሰኑት ታጋቾች ቢለቀቁም 150 ያህሉ አሁንም በሐማስ እጅ እንደሚገኙ ይነገራል፡፡
አሁን ግን ሐማስ የእስራኤል የጋዛ ጥቃት ካልቆመ አንድም ታጋች አልለቅም ማለቱ ተሰምቷል፡፡
በኢራቅ ባግዳድ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ አነጣጥሮ በተፈፀመው የሮኬት ጥቃት የተጠረጠሩ በርካታ የመንግስት የፀጥታ ባልደረቦች መያዛቸው ተሰማ፡፡
በኤምባሲው ላይ በተተኮሰው ሮኬት አንዳችም ጉዳት አለማጋጠሙን ቃል አቀባዩ መናገራቸውን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡
ያም ሆኖ ጥቃቱ መሰንዘሩን አሜሪካ የስድብ ያህል ቆጥራዋለች ተብሏል፡፡
ከጥቂቱ ጋር በተያያዘ እስከ ትናንት ምሽት 13 የኢራቅ መንግስት የፀጥታ ባልደረቦች መያዛቸው ታውቋል፡፡
ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችም እየተፈለጉ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በባግዳድ የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ሲሰነዘሩ ለነበሩ መሰል ጥቃቶች ከኢራን ጋር ቁርኝት አላቸው የሚባሉ ታጣቂ ቡድኖች ስማቸው በክፉ ሲነሳ ቆይቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ሺአ አል ሱዳኒ ስልጣን ለመጨበጥ የበቁት በአፍቃሪ ኢራን የፖለቲካ ጥምረት ድጋፍ መሆኑ ይነገራል፡፡
የካሪቢያኗ አገር ሔይቲ የፖሊስ አዛዥ ፍራንትዝ ኤልቤ ከኬንያ የፖሊስ ሹሞች ጋር እየተነጋገሩ ነው፡፡
የሔይቲው የፖሊስ አዛዥ በኬንያ በጉብኝት ላይ እንደሆኑ አናዶሉ ፅፏል፡፡
ሔይቲ በተደራጁ የወሮበላ ቡድኖች በሥርዓተ አልበኝነት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ከወደቀች መቆየቷ ይነገራል፡፡
ኬንያ ደግሞ ወደ ሔይቲ ህግ እና ሥርዓት አስከባሪ 1000 ፖሊሶችን ለማዝመት ቀደም ብላ ቃል ገብታለች፡፡
ሆኖም የኬንያ ፍርድ ቤት የአገሪቱን ፖሊሶች የሔይቲ ስምሪት አግዶት እንደሚገኝ ዘገባው አስታውሷል፡፡
የኬንያንም ሆነ የሌሎች ሀገሮችን ፖሊሶች የሔይቲ ስምሪት የፀጥታው ምክር ቤት ካፀደቀው ቆይቷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments